በያዝነው ሳምንት የሦስት ሙዚቀኞች ስራ በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል ይለቀቃል

ሰዋሰው ዜና – ጥር 8/2015 ዓ.ም. 

የሁለት ዓመታት መተግበሪያውን የማበልጸግ ሂደቱን አጠናቆ መስከረም 2015 ዓ.ም. በይፋ ስራ የጀመረው ሰዋሰው መተግበሪያ በያዝነው ሳምንት ሁለት የሙዚቃ ቪድዮ እና አንድ ግማሽ አልበም (ኢፒ) ይለቃል። ከ100 በላይ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያስፈረመው ሰዋሰው በሙዚቃ ባለሙያዎች እና በአድማጮች ዘንድ ያለው ተቀባይነት እያደገ ስለመምጣቱ የቁጥር መረጃዎች ያሳያሉ። በመቀዛቀዝ ላይ የነበረውን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በማነቃቃቱም በብዙዎች ተመስግኗል።

sewasew multimedia

የሙዚቃ ቪድዮአቸው በዚህ ሳምንት ለዕይታ የሚበቃው ድምጻዊያን ከዚህ በፊት የሙዚቃ ስራቸውን በመተግበሪያው አማካኝነት የለቀቁት ግርማ ተፈራ እና ቴዎድሮስ ሞሲሳ ናቸው። ግማሽ አልበም (ኢፒ) ስራውን በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል በያዝነው ሳምንት የሚያደርሰው ደግሞ በአማርኛ እና ኦሮምኛ ነጠላ ዜማዎቹ የሚታወቀው ድምጻዊ ኤቢ ማን ነው። 

ከ10 ቀን በፊት “ግን የትሀገር?” የተሰኘውን 15 ዘፈኖች የያዘ አልበም በሰዋሰው በኩል ለአድማጮቹ ያደረሰው ግርማ ተፈራ ካሳ “መርጦ ማፍቀር የለም” ለተሰኘው ሙዚቃ የቀረጸውን የሙዚቃ ቪድዮ በሰዋሰው በኩል ለሕዝብ ያደርሳል።

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳም በተመሳሳይ “ወድጄሽ” የሚል መጠሪያ ላለው ሙዚቃው የተሰራውን የሙዚቃ ቪድዮ ለአድማጭ እንደሚያደርስ ታውቋል። ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ተክኖሎጂያዊ መፍትሔ ያመጣው ሰዋሰው መተግበሪያ በአፕ ስቶር እና በፕሌይ ስቶር ላይ በነጻ የሚገኝ በኢትዮጵያውያን የበለጸገ መተግበሪያ ነው። ጥራት ያላቸውን የሙዚቃ ሥራዎች እያገበያየ የሚገኘው “ሰዋሰው” ወደፊት ፖድካስቶች፣ ድምጸ መጻሕፍት (የመጽሐፍ ትረካ)፣ የሁነት ዝግጅቶች ላይ ለመሰማራት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል።      

Recent Posts