እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ

በዳዊት አርአያ

ሙዚቃ ለኔ የስሜት መግለጫ ቋንቋዬ ነው ሀዘን ደስታዬን የምገልጽበት፤ ሙዚቃ ለኔ ጓደኛዬ ነው

እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ

አዲስ አበባ ከተማ ታህሳስ 14 ቀን 1915 ዓ.ም. የተወለዱት እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ “የሙዚቃ ፍቅር በውስጤ ያደረው ገና በልጅነቴ ነው።” ይላሉ። የእናታቸው ወ/ሮ ካሳዬ የለምቱ በገና ደርዳሪነት፣ የአባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ የክላሲካል ሙዚቃ ወዳጅነት ያደረባቸውን የሙዚቃ ፍቅር እንዲገፉበት እንዳበረታታቸውም አልሸሸጉም።

 

“እናቴ ትነግረኝ እንደነበረው አባቴ በአገረ-ገዥነት ተሹሞ ይሠራ በነበረበት ወለጋ ጠቅላይ ግዛት የኦሮሞ ብሔረሰብ አዳኞች ግዳይ ጥለው እየዘፈኑ በቤታችን በኩል ሲያልፉ በዜማቸው እየተማረኩኝ ተከትያቸው እሄድ ነበር።”

ስደትና ሙዚቃ

እማሆይ ጽጌ ማርያም (የውብዳር ገብአሩ) ከኢትዮጵያ ለትምህርት የተላኩት የ6 ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር። ከእህታቸው ዶ/ር ስንዱ ገብሩ ጋር ስዊዘርላድ እስከሚገቡበት ጊዜ የነበረውን ሂደት እንደማይረሱት ተናግረዋል።

 

“የስድስት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር ከታላቅ እህቴ ከዶ/ር ስንዱ ጋር ወደ ስዊዘርላንድ ለትምህርት የተላኩት። ከአገራችን የወጣንበት ዛሬም ድረስ አልረሳውም። ከጅቡቲ ጉዞ በጀመርንበት ጀልባ ላይ የተሳፈርን ብቸኛዎቹ ጥቁሮች እኛ ነበርን። በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ሰማዩ ላይ የፈካችውን ሙሉ ጨረቃና ማዕበል የሚንጠውን ባህር በተመስጦ ነበር የምመለከተው። ከዚያ በመነሳት ነው በኋላ ላይ “የባህር ላይ ዘፈን” (Song of the sea) የሚለውን ሙዚቃ የደረስኩት። ፍላድ ከተባሉ ካህን ጋር ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየን በኋላ ኑቻቴል አቅራቢያ ወደሚገኘው ሞንትሚሬል የተባለ ትምህርት ቤት ገባን። በትምህርት ቤት ውስጥ በዕድሜ በጣም ትንሽ እኔ ብቻ ነበርኩ። እንድትንከባከበኝ የተመደበችልኝ ሶኤር ማግዳ የተባለች የግል ነርስ ነበረችኝ።አንድ ቀን የቫዮሊን ድምፅ ሰማሁና የገና አባት ቫዮሊን እንዲሰጡኝ ደብዳቤ ጻፍኩላቸው። ፒያኖ ማጥናት የጀመርኩት በስምንት ዓመቴ ሲሆን የመጀመሪያ የሙዚቃ ኮንሰርቴን ያቀረብኩትም የአስር ዓመት ልጅ ሳለሁ ነው።

ከእኔ ክፍል አጠገብ በሚገኝ ክፍል ውስጥ አንድ ፒያኖ ነበር። አንዲት ልጅ ወደ ክፍሉ እየመጣች ፒያኖ ትለማመድ ነበር።

አንድ ቀን ልጅቷ ልምምዷን ጨርሳ ስትወጣ ገባሁና የፒያኖውን ቁልፎች መነካካት ጀመርኩ። “ምን ሙዚቃ ነው እየተጫወትሽ ያለሽው?” ብዬ ስጠየቅ “ማዕበል!” ስል መለስኩላቸው።

ምናልባት በውስጤ የነበሩ ምስቅልቅል ስሜቶችን ማንፀባረቄ ይሆናል። በኋላ ላይ “ማዕበል” የሚል ሙዚቃ ሰርቻለሁ።

ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ እቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት ገባሁ። ጎን ለጎንም በአንዲት አሜሪካዊት መምህርት አማካይነት ፒያኖ መማር ጀመርኩ። ፒያኖ መማር የመረጥኩት የሙዚቃ መሣሪያው እንደ ቫዮሊን ሌላ አጋዥ የማያስፈልገውና ለብቻዬ መጫወት የምችለው በመሆኑ ነው። የአስር ሦስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ጣሊያን አገራችንን ወረረች። ቤተሰባችንም በፖለቲካ እስረኛነት ወደ ጣሊያን የአሲናራ ደሴት ወህኒ ቤት በግዞት ተወሰደ። በኋላም ሜርኮሊያኖ ወደ ተባለ ቦታ ተዘወርን። እዚያ ሳለሁ ነው ከካቶሊክ ሲስተሮች ጋር ሆኜ ኦርጋን መጫወት የተማርኩት። ከሦስት ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስን። የኔ ምርጫ ግን እዚያው ቀርቶ ሙዚቃ መማር ነበር።”

ካይሮ

ሙዚቃን በብቃት የመማር ፍላጎታቸው በሐገር ውስጥ እንሰማይሳካ ያወቁት እማሆይ የውጭ እድል ማፈላለጋቸውን ቀጠሉ። በወቅቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ባልደረባ ሆነው ለ2 ዓመታት ቢጥሩም ፍላጎታቸው ሙዚቃ ብቻ ሆነ። በአባታቸው አማካኝነት ለንጉሡ ያስጠየቁት የትምህርት እድል ተፈቅዶ ካይሮ ተላኩ።

“ቫዮሊንና ፒያኖ ተምሬ ከፖላንዳዊቷ የቫዮሊን መምህሬ ዲፕሎማ የተቀበልኩትም በካይሮ ነው። በወጣትነት ሕይወቴ ከፍተኛውን ደስታ የተጎናጸፍኩበት ጊዜ ይሄ ነበር። በሃያዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበርኩ ሲሆን በየዕለቱ ቫዮሊን ለአራት ሰዓታት ፒያኖ ደግሞ ለአምስት ሰዓታት ያህል እጫወታለሁ። በየመሃሉ ደግሞ ወደ ሬስቶራብቶችና ፊልም ቤቶች እየሄድኩ እዝናና ነበር። ነገር ግን የካይሮን ሙቀት መቋቋም አቅቶኝ ታመምኩ። ወደ ቀዝቃዛ ሥፍራ እንድሄድም ተመከርኩኝ። ያኔ ትንሽ የዋህ ስለነበርኩ ፖላንዳዊዋ የቫዮሊን መምህሬ ኮንቶሮዊች የለገሰችኝን ምክር ተቀብዬ ፒያኖ የመማር ተጨማሪ ዕድል ወደ ማላገኝበት አዲስ አበባ ተመለስኩ።”

ሐዘን እና ድባቴ

 “አዲስ አበባ እንደመጣሁ በእንግሊዝ ነፃ የሁለት ዓመት የትምህርት ዕድል ባገኝም የጉዞ ፈቃድ ተከለከልኩ። ይሄኔ ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ገባሁ። ቤተሰቦቼ ለበዓል ወደ ክፍለ ሀገር ሄደው ለብቻዬ ስለነበርኩ ለሁለት ሳምንት ያህል ከቡና በቀር እህል በአፌ አልዞረም። ከሄዱበት ሲመለሱ በጸና ታምሜ አገኙኝና በአፋጣኝ ሆስፒታል ወሰዱኝ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ብሆንም የምሞት ስለመሰለኝ እንዲያቆርቡኝ ጠየቅሁ። ከቆረብኩ በኋላ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። ከ24 ሰዓት በኋላ ስነቃ አስተሳሰቤ ሁሉ ተቀይሮ የማላውቀው አይነት ሰላም ተሰማኝ። ጊዜዬን በቤተክርስቲያን ማሳለፍ ጀመርኩ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውብ መዝሙሮችም ቀልቤን ማረኩት። ትምህርቴንና ሙዚቃ ትቼ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠለልኩ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም በክብር ዘበኛ ውስጥ በውጭ ቋንቋዎች ጽሁፍ ሥራ ጀመርኩ።

ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1940 ዓ.ም በ25 ዓመቴ ለማንም ሳልናገር ወሎ ግሸን ማርያም ለንግስ በዓል ሄድኩኝ።”

ምንኩስና

 “…ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼ ከዓለም ተነጠልኩ። እቅዴ በጫካ ውስጥ ባህታዊ ሆኜ ኑሮን ለመግፋት ነበር። ግሸን ማርያም እንደደረስን መነኮሳቱን ቀሳውስቱንና አቡነ ሚካኤልን አገኘሁ። ለመመንኮስ እንደመጣሁ ለአቡነ ሚካኤል ነገርኳቸው። እርሳቸው ግን ፈቃደኛ አልነበሩም። እኔም ውሳኔዬ መሆኑን አስረግጬ ነገርኳቸው። እናትና አባትሽ ሳይፈቅዱ አይሆንም ብለው ነበር። እኔም በማቲዎስ ወንጌል ምእራፍ 10 ቁጥር 34 ያለውን ጥቅስ ጠቀስኩላቸው። “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም…” እኔ ስለራሴ መወሰን እችላለሁ በማለት ጠንከር ብዬ ተናገርኳቸው። በሀሳቤ የፀናው መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ተስማሙ። መስከረም 21 ቀን 1940 ዓ.ም. በ25 ዓመታቸው የውብ ዳር የተሰኘውን ዓለማዊ ስያሜ ጥለው እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ በሚል የምንኩስና ስም መነኮሱ።”

የመጀመርያው ሙዚቃ

 “ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ አራት አስደሳች ዓመታትን ጎንደር ውስጥ አሳለፍኩ። ሥራዬ ሁልጊዜ ማህሌት መስማት ነው። አንዳንዴ እንደውም ማህሌት ለመስማት ስል ሌሊቱን ሙሉ ቤተክርስቲያን ውስጥ አድራለሁ፤ በጣም ድንቅ ነበር።

አሮጌ ፒያኖ ስለነበረኝ እዚያ እየተጫወትኩ ሙዚቃ እደርሳለሁ። ዜማ ለመማር አገር አቋርጠው ወሎ ድረስ በመጡ ምስኪን ዲያቆናት ልቤ ተነካ። ቁራሽ ፍለጋ ቀፈፋ መውጣትና ውጭ ቤተክርስቲያኑ ደጅ ላይ ማደር ነበረባቸው። አንድ ነገር ላደርግላቸው ፈለግሁ። እናም አንድ ሙዚቃ አስቀረጽኩና ገቢው ዲያቆናቱን ለመደገፍ ዋለ።”

 የኢየሩሳሌም ጉዞ

 “ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም የሄድኩት በ1947 ዓ.ም. ከእናቴ ጋር ሲሆን ለሁለት ወራት ቆየሁ። በ1959 ዓ.ም. ተመልሼ ወደ ኢየሩሳሌም ሄድኩና ለአምስት ዓመታት ያህል ኖርኩ። በ1964 ዓ.ም እናቴ ብቻዋን ስለነበረች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየችበት እስከ 1976 ዓ.ም. ድረስ አብሬያት ኖርኩ። በፓትርያሪክ ጽሕፈት ቤት የማገኘው ደሞዝ ለአዲስ አበባ ኑሮ አልበቃ ሲለኝ ተመልሼ ኢየሩሳሌም ገባሁ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የምኖረው በኢየሩሳሌም ነው። መንፈሳዊ ሀገሬ በሆነችው ኢየሩሳሌም እኖር ዘንድ የፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነም ደስተኛ ነኝ።”

የረቂቅ ሙዚቃ አልበሞች

“ስድስት የሙዚቃ አልበሞችን አሳትሜ ለአድማጭ አቅርቤያለሁ። በኢትዮጵያና በኢየሩሳሌምም ሁለት የሙዚቃ ኮንሰርቶች አቅርቤያለሁ። አንድ ተጨማሪ አልበምም ኢትዮፒክስ በሚል መጠሪያ በፍራንሲስ ፋልሴቶ ከሚታተሙት ተከታታይ የሙዚቃ አልበሞች ውስጥ ተካቶልኛል። “ሆምለስ ወንደረር” እና “ሶንግ ኦፍ ዘ ሲ” የተሰኙትን ሁለት አልበሞቼን ያስቀረጽኩት በ1955 ዓ.ም. ጀርመን ውስጥ ለስድስት ወራት በቆየሁበት ጊዜ ነበር። የመጀመሪያውን አልበም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ሁለተኛውን ደግሞ አማቼ ጄነራል ከበደ ገብሬ ነበሩ የገንዘብ ድጎማ አድርገው ያሳተሙልኝ። (ጀነራል ከበደ ገብሬ የታላቅ እህታቸው የወ/ሮ ደስታ ገብሩ ባለቤት ነበሩ) እውቁ የሙዚቃ ሊቅ ሞዛርት በተጫወተበት ፒያኖ የመጫወት ዕድል ሳገኝ በደስታ ነበር የተዋጥኩት።”

 

የእማሆይ ጽጌማርያም ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ የመጨረሻ አልበማቸው እንደሚወጣ ተነግሯል። “ኢየሩሳሌም” የተሰኘ መጠሪያ ያለው አልበሙ በሲዲ እና በዲጅታል ለአድማጮች የሚደርስ ሲሆን 10 የፒያኖ ትራኮችን ይዟል። ከሙዚቃዎቹ መካከል “ወለጋዬ ለቅሶ ይብቃሽ” የተሰኘ ርዕስ ያለው ሙዚቃ እንደሚገኝበት ታውቋል። የሙዚቃው አሳታሚ ሚሲሲፒ ሪከርድስ ነው።

 

የአልበሞቹ ገቢ

 እማሆይ የአልበማቸውን ገቢ የሚያውሉት ለእርዳታ ነው። ከአልበሞቹ ሽያጭ የተገኘውን ገቢ በተመለከተ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር። በሦስተኛው አልበሜ ያገኘሁትን ገንዘብ እህቴ ደስታ ገብሩ ላቋቋመችው ወላጆቻቸውን ያጡ የወታደር ልጆች ማሳደጊያ ለገስኩት።

“በደርግ ዘመን ከታተመው አራተኛ አልበሜ ያገኘሁትን ገንዘብም ኢየሩሳሌም ውስጥ ያለችውን የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ለመደገፍ አዋልኩት። ዘ ቪዥነር ከተሰኘው አልበሜ ያገኘሁትን ገንዘብም በወቅቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከወዲያ ወዲህ ይል ለነበረው ኢጂኤም ፋውንዴሽን ድጋፍ አድርጌበታለሁ። ሶቨኔርስ የተሰኘ ስድስተኛ አልበሜ የተገኘው ገቢም በኢየሩሳሌም ለሚገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚውል ነው።”

ስለሙዚቃዎቻቸው ከተናገሩት

“…የመጀመሪያ ሥራዎቼን ሳስቀርጽ ኢትዮጵያውያን ላይወዱት ይችላሉ የሚል ግምት ነበረኝ። ግን ደግሞ ሳልሰራው ቀርቼ ሙዚቃዬ ቀልጦ እንዲቀር አልፈለግሁም። 

አልበሙ ሲወጣ ባልጠበቅሁት ሁኔታ ሰዎች ወደዱት ብዙዎቹ ዘ ሆምለስ ወንደረር የሚለውን ሙዚቃዬን ሲሰሙ እንደሚያለቅሱ ይነግሩኛል። ሁሉም በሕይወት ዘመኑ ሲታገል የኖረ ነው። ሙዚቃዬ የሰዎችን ስሜት ኮርኩሯል ማለት ነው። ይሄ ደስታን ያጎናጽፈኛል። የመጀመሪያ ሥራዬን ንጉሡ በሬድዮ ሳያሰራጩት አይቀሩም ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ዘ ሆምለስ ወንደረርን የአስርና የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ሆነው እንደሰሙትና የሙዚቃው ደራሲ ማን እንደሆነ ጨርሶ እንደማያውቁ የሚነግሩኝ ሰዎች አሁንም ድረስ ይገጥሙኛል።

… የሙዚቃ ሥራዎቼን ለአድማጭ የማድረስ ፍላጎቴን እኔ ከመረጥኩት መንገድ በተለየ ጎዳና ተጉዤ እውን እንዳደርግ የፈቀደልኝ የፈጣሪ ፀጋ ነው። የተከተልኩት ጎዳና “መጀመሪያ የእግዚአብሔርን መንገድ ፈልግ፤ ከዚያም የፈለግኸው ሁሉ ይሰጥሃል” የሚለውን የወንጌሉን ቃል የሚያንጸባርቅ ነው። ህይወቴ በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ ነበር። መንፈሳዊና ሰላማዊ ሕይወት እመራ ዘንድ ታድያለሁ። እና ደግሞ በቸርነቱ ሙዚቃን ተቀብቻለሁ።

ዝና የሚያጓጓኝ ሰው አይደለሁም። እሱ የወጣቶች ስሜት ነው። የምፈልገው ነገር ቢኖር ሙዚቃዬ ባክኖ እንዳይቀርና ለሁሉም ተዳርሶ እንዲሰማ ብቻ ነው። ሙዚቃዎችን የምጽፈው ከላቀ መነሸጥ ተነስቼ ነው። አንዳንዴ ሙዚቃ ድንገት ከውስጤ ይፈልቃል። እንዲህ ሲሆን የሙዚቃው ሃሳብ ከልቦናዬ ሳይጠፋ ፈጥኜ መጻፍ አለብኝ። አንዳንዴ ደግሞ በውድቅት ሌሊት ከእንቅልፌ እነቃና የመጡልኝን ስንኞች ሳልረሳቸው በወረቀት ላይ አሰፍራቸዋለሁ። ሙዚቃ ከራስ ጋር የመወያያ መንገድ ሆና ልታገለግል ትችላለች። ሃዘን ገብቶ ዙሪያ ጨለማ ሲሆን ሙዚቃ በዙሪያ ፍንትው የምታደርገው የራሷ ብርሃን አላት።”

የመጀመርያው ኮንሰርት

“የመጀመሪያ የሙዚቃ ኮንሰርቴን ያቀረብኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ጊዜውም በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር። በወቅቱ በተከሰተው የረሀብ አደጋ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማሰባሰብ ታልሞ በተዘጋጀው በዚህ ኮንሰርት ላይ ቬትሆንን ፓቲክ የተሰኘ ሙዚቃና የራሴን ሆምለስ ወንደረር ተጫውቻለሁ። ከኮንሰርቱ በኋላ ከእህቴ ደስታ ጋር ወደ ወሎ አቅንቼ ነበር። በረሀብ ተጎድተው በአጥንታቸው የቀሩ እናቶችንና በውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ የሚሰቃዩ ህፃናትን ተመለከትኩ። ከዚያ አሰቃቂ ተሞክሮ በመነሳት ነው  ‘የድርቅ እልቂት’ (famine disaster) የሚለውን ሙዚቃዬን የደረስኩት።”

 ምንኩስና እና ፒያኖ

“በርካታ ችግሮችን ተጋፍጫለሁ። በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፒያኖ መጫወቴንና ሙዚቃ መሥራቴን ይነቅፉት ነበር። “ፒያኖ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ባህላዊ መሳሪያ አይደለም” በማለት ተቃውሟቸውን ይገልጹ ነበር። እኔም ታዲያ “ፈጣሪን ለማመስገን እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም መሳሪያ መጫወት መልካም ነው” እላቸው ነበር። ከቤተክርስቲያኗ ግን በዚህ ጉዳይ ተቃውሞ ገጥሞኝ አያውቅም። ለሚተቹኝም ሆነ ሥራዬን ለሚያንኳስሱ ሰዎች ደንታ አልነበረኝም። ለእንዲህ ያሉ ነገሮች ጆሮዬን ሳልሰጥ ጉዞዬን ወደፊት ቀጠልኩ። ለዚህም ፈጣሪዬን ማመስገን ይገባኛል።”

የታተሙ ጥራዞች

ለእማሆይ ክብር ሐምሌ 28 ቀን 2013 እ.ኤ.አ የሙዚቃ ኮንሰርት በኢየሩሳሌም ተዘጋጅቶ ነበር። ከመጋቢት ወር ጀምሮ የባህል ወቅት (Jerusalem Season Of Culture) በበጋ ወራት ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በእማሆይ የሕይወት ታሪክና የሙዚቃ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮረ ነበር። መጻሕፍትም ታትመውላቸዋል።

1ኛ/ የእማሆይ የሕይወት ታሪክ

2ኛ/ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው ይዘት ናዳቭ ሃቬር እንደገለጸው

3ኛ/ የኢትዮጵያ ክርስትያኖች ታሪክ በኢየሩሳሌም

4ኛ/ ሥዕላዊ መግለጫዎችን የያዘ…በሦስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ እንግሊዝኛና ዕብራይስጥ) ባለ 120 ገጽ አንድ ወጥ መጽሐፍ

ሌላው የእማሆይን የሙዚቃ ድምፅ ምልክት

(Musical notes) የያዘ 146 ገጽ መጽሐፍ ናቸው።

እነዚህ መጽሐፍት የኢየሩሳሌም ከንቲባ የተከበሩ ኒር ባርካት በተገኙበት የኢትዮጵያ ቅርስና ሀብት በሆነው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከመቶ ዓመት በፊት ባሰሩት ቤተመንግስት አሁን የእስራኤል ራዲዮ ድምፅ በሚገለገልበት ቦታ በደመቀ ሁኔታ ሐምሌ 28 ቀን 2013 እ.ኤ.አ ተመርቋል።


ምንጭ

  • ተምሳሌት እጹብድንቅ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች፡- ሜሪ-ጄን ዋግልይ
  • የሁለት ዓለም ሰው፡- ሰዋሰው ብርሃኑ ደስታ

Recent Posts