ጥምቀት እና ሙዚቃ

በዳዊት አርአያ

በኢትዮጵያ በድምቀት የሚከበሩት አብዛኛዎቹ በዓላት መሰረታቸው ሀይማኖታዊ ነው። ቡሄ፣ ገና፣ ፋሲካ፣ አረፋ፣ መስቀል፣ መውሊድ፣ አሸንዳ፣… እያልን ብንዘረዝር የቀደመ አባባላችንን ይበልጥ ያጠናክርልናል።

የክብረ በዓላቱ መነሻ ሐይማኖታዊ ይሁን እንጂ አከባበሩ ከባህላዊ ክዋኔ ጋር የተቀየጠ ነው። መሰረታዊውን ሐይማኖታዊ አስተምህሮ ሳይለቅ በባህላዊ እንቅስቃሴዎች ይደምቃል። እንደየስፍራው፣ እንደ ኑሮ ዘይቤው እና አስተሳሰቡ በሁሉም ዘንድ ይከበራል።

የዛሬው የዘመን እና ዘፈን ዝግጅታችን ትኩረት፡- በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ስለተመዘገበው፣ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ካሏት ሁለት የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ስለሆነው፣ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘት ስላለው፣… የጥምቀት በዓል ነው። በዓሉን በሀያማኖታዊ አስተምህሮ ትተን ባህላዊ ክዋኔዎቹን ተከትለን በዘፈን መነጽር ልንመለከተው እንጥራለን።

ከጥር 10 የሚጀመረው የጥምቀት በዓል እንደየአካባቢው ሁኔታ ጥር 21 ይጠናቀቃል። በከተራ ተጀምሮ በአስተርዕዮ ማርያም ፍጻሜውን ያገኛል። የበዓሉ ዋነኛ ክዋኔ የሆነውን የጸበል ርጭት ለማከናወን ይቻል ዘንድ ታቦታቱ ወደ ውሃማው ስፍራ ከሚጓዙበት እለት አስቀድሞ የአካባቢው ወጣቶች እና የደብሩ አገልጋዮች ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት ዝማሬ ከመለማመድ፣ አካባቢዎችን ከማጽዳት፣ አልባሳት ከመግዛት ወይም የክት የሚሉትን አጥቦ ከማሰናዳት ነው።

ተመሳሳይ መልእክት እና ቀለም ያላቸው አልባሳትን በማሰራት በደቦ የማጌጥ ተግባርም ቀስ በቀስ ያደገ ነገር ግን ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት የሰጠ ነው።

ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ

በጥምቀት እርድ የሚከናወን ቢሆንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ግን ለታቦቱ ሽኝት፣ ለዝማሬው፣ ለጭፈራው እና ለጨዋታው ነው። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዲል ሐገርኛ ባህሉ፣ ሁሉም አምሮ ደምቆ ለአደባባይ የሚበቃበት ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተሞች እየተመለከትነው የምንገኘውም የቀደመውን ያስቀጠለ፤ ነገር ግን አዲስ ባህልን የፈጠረ ነው። ከ15 ዓመታት የማይበልጠው ታቦታቱ በምንጣፍ እንዲራመዱ የማድረግ ባህል በጥቂት መንደሮች ተጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ለመስፋፋት የበቃ ነው። ይህ ውብ ክዋኔ ወጣቶቹ ለነገሩ ያላቸውን መሰጠት የሚያሳይ በጎ ተግባር በመሆኑ ክብር ይገባዋል።

በዓላትን መሰረት ያደረጉ ዘፈኖች በርካታ ናቸው። አንዱን በዓል ብቻ በማንሳት የበዓሉን ልዩ ነገሮች የሚዘፍኑ እንዳሉ ሁሉ ሁሉንም በጅምላ እያነሱ እንኳን ደረስን፣ እንኳን ደስ አለን የሚሉም አሉ። ለምሳሌ የሐመልማል አባተ “እንኳን አደረሳችሁ” ለሁሉም በዓላት ልንጠቀምበት የምንችል የበዓል ዘፈን ነው። የታደሰ መከተ “ሚሻ ሚሾ” ለፋሲካ ብቻ የሚደመጥ የበዓል ዘፈን ነው። እንዲህ እያለ ሁሉም በዓላት ተዘፍኖላቸዋል። በዓማርኛ ቋንቋ የተዘፈኑ የጥምቀት ዘፈኖችን ለመሰብሰብ በሞከርንበት ጊዜ ግን የይሁኔ በላይን እና የታደሰ መከተን ሙዚቃዎች ከፊትለፊት እናገኛቸዋለን።

አንድም በጥምቀቱ አንድም በከተራው

ዘንድሮስ ሙገሳ ያንቺ ነበር ተራው

ድምጻዊ ግዛቸው ተሾመ “ነይ መላ” በሚለው ዘፈኑ ውስጥ የተካተተ መንቶ ነው። በዚህ ዘፈን ውስጥ ያለው አፍቃሪ ገጸባህርይ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ የሚደመጠው ውዳሴ፣ ጭብጨባ እና እልልታ ለወደዳት ሴት የሚሰጥ ይመስለዋል።

Traditional Ethiopian Music Instruments

እንደኔ ያለውን ወስዶ እንዳንቺ ካለው

ከየትም ያለምዳል ፍቅር ሐገር የለው

ያለላትን ሴት የጥምቀቱ እድምተኛ የከተራው አድማቂ በሙሉ ያጨበጨበላት ይመስለዋል። ዝማሬውም ጭፈራውም ለሷ ይመስለዋል ለዚህም ነው።

አንድም በጥምቀቱ አንድም በከተራው

ዘንድሮስ ሙገሳ ያንቺ ነበር ተራው

የሚላት።

ቀደም ያሉ አብዛኛዎቹ ድምጻዊያን ስለዘፈን ጅማሯቸው በሚሰጧቸው ቃለ መጠይቆች “መነሻዬ የጥምቀት በዓል ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የመጀመሪያ የሕዝብ መድረካቸው ለሆነው ጥምቀት ያቀነቀኑት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከሌሎች በዓላት ጋር ተደምሮ ወይም ስለ ሐገር በሚዘፈኑ ዘፈኖች ግን ጥምቀት ተደጋግሞ ተነስቷል።

ዘና ዘና ፋሲካ ነውና

ዘና ዘና ለጥምቀት ለገና  

(ታደሰ መከተ ፈካ ፈታ በሚለው ዘፈኑ)

ከቅንጭብ ገለጻዎች ባሻገር ጥምቀትን ርዕሰ ጉዳይ ካደረጉ ዘፈኖች መካከል ለበርካታ ዓመታት በጥምቀት በዓላት ሰሞን የሰማነው የይሁኔ በላይ “ዘገሊላ” ነው።

የገና የጥምቀት ሲወጣ ታቦቱ

ጸበሉን ተጠምቀን ባህረ ጥምቀቱ

ወርውሬ የመታሁት ጥላሽን በእንቧይ

ደግሞ ባንቺ በኔ ከልካይ አለን ወይ

የገጠሩን አከባበር በጥሩ ቋንቋ፣ ምስል ከሳች በሆኑ ቃላት ገልጾታል። በአንዳንድ አካባቢዎች ሴቲቱን ከጅዬሻለሁ ለማለት ጥቅም ላይ የሚውለው ሎሚ በእምቧይ ተተክቷል። (እምቧይ ሎሚ የሚመስል ነገር ግን የማይበላ ፍሬ ነው።) ቀደም ብለን እንደምናውቃቸው ዘፈኖች የሎሚ ውርሰራው ግልጋሎት ላይ የዋለው ደረትን ሳይሆን ጥላን ለመምታት ነው። ከዚህ የምንረዳው የውርወራው ዓላማ ቅስቀሳ ወይም አለሁ ለማለት እንጂ ለአዲስ የክጀላ ጥያቄ አለመሆኑን ነው።

እለቱ ጥምቀትም አይደል? ሁሉ አምሮ ደምቆ ለአደባባይ የሚበቃበት፣ የሚተያይበት፣ የሚተጫጭበት፣ ለዚያም ነው “ደግሞ ባንቺ በኔ ከልካይ አለን ወይ” ማለቱ።

ይህንን ዘፈን ማድመጥ የሚገባን የገጠሩን አኗኗር በማሰብ ነው። የተራራቀ መንደር ውስጥ የሚኖሩ፣ እንደዚህ ዓይነት አሰባሳቢ በዓላት ካልተፈጠሩ በቀር በቀላሉ ለመተያየት አዳጋች የሚሆንባቸው ቀደምት የገጠር መንደሮች፣… ከኢንተርኔት እና ከስልክ ብቻ ሳይሆን ከደብዳቤም ዘመን ቀድሞ…

ባህላዊ ክዋኔውን በወቅቱ እስከሚዘወተረው የልብስ እና የጌጥ ዓይነት ድረስ የተካተተበት ዘፈን ለመጪው ዘመን ታሪክን የማቆያ አንድ ብልሃት ይመስላል። “ወንዝ አይፈሬ ቀሚስ”፣ “ትፍትፍ መቀነት”፣ “ጉንፍ”፣ “አምባር”፣ “መስቀል”፣ “ማተብ”… የዘፈኑ አንድ አካል ናቸው።

ወንዝ አይፈሬው ቀሚስ የተሸነሸነው

ትፍትፉ መቀነት ወገቡን የዞረው

ልክ እንደ ጉንፏ አውሎ አሳደረው

ለመታየት አደባባይ የወጣችውን እንስት አትዩብኝ የሚለው ገጸ ባህርይ “የጥዋት እጣዬ” የሚላትን ወዳጁን የዘገሊላ እለት እንድትመጣ ሲማጸን ለአስተርዕዮ ማርያም እንደማይቀር ቃል በመግባት ነው። የዘፈኑ አሰነኛኘት የጊዜ ችግር ያለበት ይመስላል። የቀደመው አገላለጽ ተናጋሪው ወይም ዋናው ገጸ ባህሪ ጥሪውን ያቀረበው ከሁለቱም በዓላት በፊት ይመስላል። እኔ ለአስተርዕዮ ማርያም አልቀርም አንቺም የዘገሊላ እለት ነይልኝ ሲል ቀጠሮ የሚይዘው ቀደም ባለው ቀን ነው። በሌሎቹም ስንኞቹ የቀደመ እውቂያ ካለው ወዳጁ ጋር የሚያወራ ይመስላል። ተከታዮቹ ስንኞች ግን የቀደመውን አካሄድ ያፈርሳሉ

የዘገሊላ ለት አይቼሽ ደክሜ

ልክ እንደ ታቦቱ አንቺን ተሳልሜ

ያአስተርዕዮ ማርያም መጣብኝ ህመሜ

ገጸ ባህሪው የት ነው የቆመው? ከበዓሉ በፊት? ከበዓሉ በኋላ? የአስተርዕዮ ማርያም ወይስ የዘገሊላ ዕለት? ግልጽ ያልሆነ ነገር ያለ ቢመስልም ነባሩን ክብረ በዓል በተለይም በገጠሩ አካባቢ ያለውን ለማሳየት ያደረገው አበርክቶ እንደ እንከን ከሚታዩት በእጅጉ ይበልጣል። የሚጠናቀቀው የበዓሉን ባህላዊ እና መንፈሳዊ ይዘቶች በሚያስተሳስሩ ስንኞች ነው።

ሆታ እና ጭፈራው

ካህናተ መዝሙር ዜማና ውረባው

ካንቺ ጋር ደመቀ ያመትባል ጨዋታው

የጥምቀት በዓል በልዩ ልዩ ቦታዎች ይከበራል። የበለጠ ደምቆ ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል የጣና ገዳማት ጥምቀት እና የጎንደር ጥምቀት ተጠቃሽ ናቸው።

ድምጻዊ ታደሰ መከተ “ተዋበች ጎንደር” ሲል ለጎንደሩ ጥምቀት እንዲህ ዘፍኗል።

sewasew multimedia

በወርሃ ጥሩ በከተራ

እልልታው ይድረስ ከዳሽን ጋራ

ወሸባው ይድመቅ በጥምቀቱ

ታቦታት ተመው አርባ አራቱ

ተዋበች ተዋበች ጎንደር – በጥምቀት

የከተማዋን ሁኔታ፣ የሕዝቡን እና የአከባበሩን ጨምሮ አብዛኛዎቹን ሂደቶች በግጥሙ ውስጥ አካቷል።

የፋሲል ግንቡ ስሩ ጸበል

ያዩት ታቦት ነው አስርቱ ቃል

እንኳን ሐገሬ የምነት ምንጩ

ሁሌም ይመጣል ደንቆት ነጩ

ተዋበች ጎንደር – በጥምቀት

እንደዚህ ባህላዊውን ከሐይማኖታዊው ጋር የሚያስታርቁ ዘፈኖች ቢለመዱ ታሪኩን እንዲህ ማቆየት ይቻላል። መልካም የጥምቀት በዓል!

Recent Posts