የአንባሰሏ ንግሥት የክብር ዶክትሬቷን ከ7 ዓመታት በኋላ ተረከበች
ሰዋሰው ዜና – ጥር 6/2015 ዓ.ም.
ከሰዋሰው መተግበሪያ ጋር ለምትሰራቸው 4 የሙዚቃ ኮንሰርቶች አልበምና የሙዚቃ ቪድዮ ከ23 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ሐገሯ የተመለሰችው አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የተሰጣትን የክብር ዶክትሬት ዲግሪዋን ተረክባለች። በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ደሴ፣ ጎንደር እና ባህርዳር ለሚኖራት የሙዚቃ ድግስ በመሰናዳት ላይ የምትገኘው አርቲስቷ የክብር ሽልማቷን የተረከበችው ከ7 ዓመታት በኋላ ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው።
ዩኒቨርሲቲው ለማሪቱ ይህንን ክብር የሰጠው በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ በማበርከቷ መሆኑ በወቅቱ ተገልጾአል። የሐገር ባለውለታዎችን ማክበር ተተኪ ባለሙያዎችን የማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑን ያመነው የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አርቲስቷ ወሎን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በሐገር ውስጥ እና በውጭ ሐገር በማስተዋወቋ፣ አለባበስ፣ ባህልና እሴቱ ለትውልድ እንዲተላለፍ በመስራቷ የክብር ዲግሪው እንደሚገባት ወስኗል።
በአድናቂዎቿ የአምባሰሏ ንግሥት፣ የቅኝቶች እናት፣ የባህል ሙዚቃ ንግሥት፣ ማሬዋ በሚሉ የፍቅር ቅጥያ ስሞች የምትጠራው ማሪቱ የመቅደላና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ ባልደረቦቿ፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት አባላት፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የክብር ዲግሪዋን ተረክባለች። አርቲስት ማሪቱ ለገሰ በክብር ዲግሪው ርክክብ ስነ-ስርአት ወቅት ለተሰጣት ክብር አመስግና ለወደፊት ስራዋም ብርታት እንደሚሆናት ገልጻለች። ከ23 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ለተደረገላት አቀባበልና ለሰጣት ክብርም አመስግናለች።
አራቱን የሙዚቃ ቅኝቶች በብቃት በመጫወት የምትታወቀው ክብርት ዶ/ር ማሪቱ ለገሰ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በተሻገረው የሙዚቃ ህይወቷ በተለይም በአምባሠልና ባቲ ቅኝቶች አጨዋወቷ ከፍ ያለ ክብር አግኝታለች። ቅኝቶቹ የስሟ መጠሪያ እስከመሆንም ደርሰዋል። ከድምጸዊቷ ልዩ መታወቂያዎች አንዱ ዓመቱን ሙሉ የባህል አልባሳትን መልበሷ ነው። የሰዋሰው መተግበሪያ የክቡር ዶ/ር ማሪቱን ወደ ሐገር መመለስ አስመልክቶ የእናት ባንክን የ200ሺህ ብር የአክስዮን ድርሻ በስጦታ እንዳበረከተላትም ታውቋል።