አዝማሪ እና የዓድዋ ድል
በዳዊት አርአያ
ሬይሞንድ ጆናስ “The Battle of adwa- African victory in the age of Empire” በተሰኘ ስመ–ጥር መጽሐፉ ስለ ዓድዋ ድል እንዲህ ሲል መስክሯል።
“የዓድዋ ድል በጦርነቱ ዋዜማ በዓለም ልእልና የነበረውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በአፍጢሙ የደፋ ክስተት ነበር።”
ሬይሞንድ ይህንን ብሎ ብቻ አያበቃም
“የኢትዮጵያ ድል አፍሪካዊው ጦር አውሮፓዊውን ጦር አሸነፈ በሚል ብቻ አልተተረጎመም” ይላል። ትርጓሜው በኢትዮጵያ ቅጥር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካም ተሻግሮ የመላው ጥቁር ህዝብ ሆኗል። “ጥቁር ሰራዊት ነጭ ሠራዊትን አሸነፈ” ማለት፡– የማይረታው ተረታ፣ የማይደረስበት ሰማይ ተዳሰሰ፣ የማይቻል ተቻለ የሚል ትርጓሜ ሰጥቷል። ሬይሞንድ ጆናስ ከፍ ብለን በጠቀስንለት መጽሐፉ መግቢያ ላይ “ዓድዋ በኔ እምነት የዓለም ቅርስና ዓለም አቀፍ ታሪካዊ ክስተት ከምንላቸው ውስጥ የሚመደብ ነው” ይላል።
በዚህ ጽሑፍ እጅግም ካልተነገረላቸው፣ ለድሉ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ከነበራቸው አዝማሪዎች መካከል ጥቂቶቹን እናነሳለን። አዝማሪ የሰላም ጊዜ ደስታ ፈጣሪ የሆነውን ያህል፣ ማኅበረሰባዊ ስህተትን ነቃሽ ነው። የጦርነት ዘመን አጀጋኝ እና ታሪክ ዘጋቢ የመሆኑን እውነት ደግሞ በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት እንሞክራለን።
ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” ሲል ባሰናዳው ድርሳን ላይ በርክሌይ የጻፈውን የጉዞ ማስታወሻ ጠቅሶ ይህንን አስፍሯል።
“በሠራዊቱ መሐል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ። በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ። አብሯቸው የሚሄደው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሯቸዋል። አዝማሪዎቹም የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ። […] የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው ጠብመንጃ እና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎች እየዘፈኑ፣ ቄሶቹ፣ ልጆቹ፣ ሴቶቹ ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ግዜ የኢጣሊያንን ጦር አሸበሩት“
የመረጃ ቅብብሎሹ እንደ አሁን ከመፍጠኑ በፊት፣ የመዝናኛ አማራጮች ቁጥር ከማሻቀቡ በፊት፣ የሕትመት እና የስርጭት ቴክኖሎጂው ከመዘመኑ በፊት፣… የኅብረተሰቡ ዐይን እና ጆሮ የሆኑት አዝማሪዎች
አንድ ካህን ለነፍስህ ይቅርታ መማጸኛ
አንድ አዝማሪ ለስጋህ መዝናኛ
በሚል ከሰማያዊው ዓለም ባልተናነሰ የምድር አስፈላጊነታቸው ተወስቷል።
ሬሞንድ ጆናስ ከፍ ብለን በጠቀስነው በእንግሊዝ አፍ የተሰናዳ ድርሳኑ የጣይቱ ብጡልን ጦር አሰላለፍ እንዲህ ገልጾታል።
“…ጣይቱ በሚመሩት ጦር ያካተቱት ታጣቂዎችን ብቻ አልነበረም። በሺህ ከሚቆጠረው ታጣቂ ጦራቸው በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠር የአዝማሪ ቡድንም አሰልፈዋል። በሰላሙ ቀን ጣይቱ ለበገና ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው፤ በዓድዋው ዘመቻም በርካታ አዝማርያን እና በገና ደርዳሪዎችን አስከትለዋል። የሙዚቀኞቹ ቡድን የጣይቱን ፈረስ እየተከተለ የዘመቻ ዘፈኖችን፣ ፉከራዎችን፣ ሽለላችን ያሰማ ነበር…”
አሁን ላለንበት ዘመን የተሸጋገሩልን የአዝማሪ ግጥሞች አብዛኛዎቹ ጀግናን ለማወደስ የተሰናኙ፣ ዜማ ለብሰው ለባለታሪኩ መልሰው የተሰጡ ቢሆኑም ባህርያቸውን ተንተርሰን በአራት ክፍል ልንመድባቸው እንችላለን። ቀስቃሽ፣ የሙሾ፣ አወዳሽ፣ ታሪክ ነጋሪ ግጥሞች በሚል።
በሺህ ከሚቆጠሩ እነዚህ ቃላዊ ግጥሞች ውስጥ በታሪክ ዘጋቢዎቻችን ልብ ውስጥ ገብተው በጽሑፍ ከተላለፉልን መካከል ምሳሌ የሚሆኑንን እየመዘዝን እንቀጥላለን።
የሙሾ ግጥሞች
በዚህ ርዕስ ጀግናው ህይወቱን ካጣ በኋላ ቋሚን ለማስተዛዘን ተገጠሙ ግጥሞች እና እንጉርጉሮዎች ይገኛሉ። በወቅቱ በርካታ ሙሾ አውራጆች የየስሜታቸውን ሊገጥሙ እንደሚችሉ ይገመታል። ከነዚያ ውስጥ እስካለንበት የጽሑፍ ዘመን ብሎም የሪኮርዲግን ዘመን ድረስ መጓዝ የቻሉትን ብቻ እያነሳሳን እንደሆነ ይሰመርበት።
የሐረርጌው ገዢ ራስ መኮንን ሞት በተሰማ ጊዜ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ማዜሙን “ታሪከ ዘመን– ዘዳግማዊ ምኒልክ” ከትቧል። የዘገቡልን ጸሐፌ ትዛዝ ገብረሥላሴ ናቸው።
ዋ አጼ ምኒልክ እግዚአብሄር ያጥናዎ
በየበሩ ቋሚ ከልካይ ሞተብዎ
አላጌ ላይ ከፊታራሪ አባ ውርጂ ሌላ ጊድን ገብሬ የሚባሉ የላስታ እና የዋግ ጦር መሪ እና እህታቸው ይገኙበታል። እህታቸው ጥይት በቀሚሷ ጫፍ እየቋጠረች ስታቀብል አብራ ሞታለች። እነዚህ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ አዝማሪ
የጊድን ነገር አይተኛም በውን
ጦር መጣ ቢሉት ይነሳል አሁን
ጊድን ገብሬ የሜዳ ዝሆን
ፈረሱን ጫኑት ይነሳ እንደሆን
የጊድን እህት ምጥን ወይዘሮ
ጥይት አቀባይ እንዳመልማሎ
አልሞተም ዛሬ ይጋልብ ከሜዳ
አኮላኮሉ የገደል ናዳ
መረጃ ካልተገኘላቸው የዓድዋ ሜዳ አዝማሪዎች መካከል ጻዲቄ አንዷ ናት። በዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” በተሰኘ ጥራዙ ላይ “…በዓድዋ ድል ዋዜማና ማግስት ከተገጠሙት ግጥሞች መካከል የትኞቹ የእሷ እንደሆኑ ለማወቅ አልተቻለም። ግን ብዙ ቀስቃሽ ግጥሞች ከመግጠሟ የተነሳ ሃኪም መረብ የተባለ የፈረንሳይ ጎብኝ ከዝነኛው የስፓርታ የጦር ሜዳ ገጣሚ ከጠርየስ (ቴርየስ) ጋር ያወዳድራታል። ፃዲቄ በዓድዋ ጦርነት ላይ ላደረገችው አስተዋፅኦ ከምኒልክ እጅ ሽልማትና የወይዘሮነት ማዕረግ ተቀዳጅታለች…” ሲል ጽፏል።
ጻዲቄ እቴጌ ጣይቱ ሲሞቱ ያወረደችው ሙሾ ከግጥሞቿ መካከል ተጠቃሽ ነው።
የመካን ቤትና ባመድ የነገደ
እቴጌ ቤትዎ ምን ጊዜ በረደ
ራቴን አብኩቼ
ምሳዬን በልቼ
መጣሁ ሰከም ብዬ
ልጅሽ አይቆጣኝ አንቺ አታይኝ ብዬ
በተከታዩ የአዝማሪ እንጉርጉሮ ያነሳነውን ንዑስ ርዕስ እንደምድም
የጎራው ገበየሁ ምናሉ ምናሉ
ያ ትንታግ ታፈሰ ምናሉ ምናሉ
እነ ደጃች ሜጫ ምናሉ ምናሉ
ተማምለው ነበር ከጦሩ ሲገቡ
አልጋውን አቅንተው ዓደዋ ላይ ቀሩ
ያ በሻህ አቦዬ፤ ያጎራው ገበየሁ ሁለቱም ያበዱ
እንቅር አይሉም ወይ አንዱ ሲሄድ አንዱ
ቀስቃሽ ግጥሞች
በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱት ግጥሞች ከጦርነቱ በፊት እና በጦርነቱ ወቅት ነዋሪውን ለማነሳሳት እና እንዳይሸሽ ለማበረታታት ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው።
ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ
በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ
የሚለው የአዝማሪ ግጥም የካቲት 22 ሌሊት የአልቤልቶኒን ጦር ፊትለፊት እየተመለከቱ እንዳ ኪዳነ ምህረት የተባለ አካባቢ ላይ ሲዜም ማንጋቱን የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ያስረዳል።
ባህር ዘሎ መምጣት ለማንም አይበጅ
እንደ ተልባ ስፍር ትከዳለች እንጂ
አትረጋም ሐገር ያለ ተወላጅ
የሚለውን ከላይ ካነሳነው ስንኝ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ግጥም ሰርጸ ፍሬ ስብሃት ጽፎት “ደቦ” በተባለው 60 ደራሲያን በተሳተፉበት ጥራዝ ላይ “የአዝማሪ ሚና ለዓድዋ ድል” በተሰኘው ጽሑፉ ጠቅሶታል። የመጽሐፉ አርታኢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው።
ያድዋን ሥላሴ ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ስርግው ገላው አዝማሪን በተመለከተ የመድረክ ንግግራቸው የአዝማሪ ግጥሞች ሰም ለበስ በመሆናቸው አመራማሪ እና ከመጠቀ ምናብ የሚፈልቁ ናቸው ይላሉ። እንደ ዶክተር ስርግው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የነበረው የዓለም ዐተያይ እና ፍልስፍና ከአውሮፓውያን የሚልቅ እንደነበር ማስረጃዎች ስለመኖራቸው አብራርተዋል። የማኅበረሰብ ስምምነቶች እና ደንቦች፣ ፍላጎቶች እና እሳቤዎች በአዝማሪዎች ይገለፃሉ። ከዜማ ጋር ተዳምሮ በግጥም የሚገለጸው ፍልስፍና በቅጡ አለመጠናቱ እንጂ የሚናገረው ነገር ቀላል አይደለም።
በጎንደር ስልጣኔ ወቅት አዝማሪነት ከፍ ያለ ልዕልና ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር። ‘ሊቀ መኳስ’ የሚል ማዕረግም ተችሯቸዋል።
ቢያብጥ ቢደነድን ቢከመር እንደ ጭድ
ደንዳናውን እንዶድ ይቆርጠዋል ማጭድ
ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ
አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ።
እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው
አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው።
ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ ዕይ
አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ።
አዝማሪዎች የሚሆነውን ቀድመው በመተንበይ ማኅበረሰቡን ያነቁበት አጋጣሚም ተስተውሏል። አዝማሪ ጻዲቄ ለመቀሌው እርቅ የገጠመችው ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል።
አውድማው ይለቅለቅ በሮችም አይራቁ
ቀድሞም ያልሆነ ነው ውትፍትፍ ነው እርቁ
አወዳሽ ግጥሞች
በአዝማሪዎች የተሰናኙት ግጥሞችን ባህርይ ተከትለን በሰጠነው ምድብ መሰረት በቀጣይነት የምንመለከተው አወዳሽ ግጥሞችን ነው። የጀግኖች ወይም የመሪዎች ውዳሴ ከላይ ባነሳነው በሙሾ ግጥሞች ላይም የሚስተዋል ቢሆንም በዚህ ምድብ ውስጥ የተካተቱት አብዛኛዎቹ ባለታሪኮች በሕይወት ባሉ ጊዜ የተባሉ ናቸው። በህይወት ለሌሉትም ቢሆን ከሐዘን በራቀ ስሜት ተገጥሞላቸዋል። ለሐገር እና ለወገን ያበረከቱት ጎልቶ ተስሎላቸዋል።
አባተ አባ ይትረፍ አዋሻኪ ሰው
ይሕንን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው
አበሻ ጉድ አለ ጣልያን ወተወተ
ዐይነ ጥሩ ተኳሽ ቧ ያለው አባተ
ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) በመድፍ ጠላትን እያሻገሩ በሚያጠቁበት ጊዜ ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ጆሯቸው ተቆርጦ ነበር። በዚህ ጊዜ አዝማሪ
ማን እንዳንተ አርጎታል የእርሳሱን ጉትቻ
የዳኘው አሽከር አባ ነፍሶ ባልቻ
በማለት አወድሷቸዋል።
“የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው የተክለ ጻድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ ደግሞ ተከታዮቹ የአዝማሪ ስንኞች ተከትበዋል።
አሉላ አባ ነጋ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተኩሶ
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ አዝማሪዎች የአልገዛም ባይነት እና የወኔ ትጥቅ አስታጣቂዎች በመሆናቸው በጣሊያን ወረራ ወቅት በብርቱ ጠላትነት ከተፈረጁት መካከል መገኘታቸውን ያነሳሉ።
በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት 40 ያህል አዝማሪዎች መርካቶ አካባቢ መረሸናቸውን Ethiopia a cultural history የተሰኘው መጽሐፍ ዘግቧል። የቀደመውን ለመበቀል እና የአሁኑን ተግባር ለመግታት ያለመው የጣሊያን ግድያ አርበኞቹ አዝማሪዎች ማኅበረሰቡን በማንቃት የነበራቸውን ጉልህ ሚና የሚያሳይ ነው።
ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት
ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት።
ታሪክ ነጋሪ ግጥሞች
በሁሉም የአዝማሪ ስንኞች ውስጥ ታሪክ አለ። የተኖረውን እውነተኛ ገድል ለጆሮ በሚጥም፣ ለቃል ንግግር በሚስማማ መንገድ አስውበው ያቀርቡታል። በፍስሃ ውስጥ በማሲንቆ፣ በሀዘን ውስጥ በእንጉርጉሮ፣ በለቅሶ ውስጥ በሙሾ፣… ይሁን እንጂ ታሪክ መንገሩ አይቀሬ ነው። በዚህ ታሪክ ነጋሪ ንዑስ ርዕስ ውስጥ የተካቱት የበለጠ ለታሪክ ነገራ ቅርበት አላቸው ለማለት በማሰብ እንጂ የሌሎቹን የታሪክ ነጋሪነት ሚና ለማሳነስ አይደለም።
ፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊው መዝገበ ሰብ በሚል ካዘጋጁት ድርሳን ላይ ደግሞ ጣልያንን ሁለት ጊዜ ስለመከቱት ጀግና ባልቻ ሳፎ እንዲህ ሰፍሯል።
አባተ በመድፉ ሃምሳውን ሲገድል
ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል
ተማራኪው ባዙቅ ውሃ ውሃ ሲል
ዳኛው ስጠው አለ ሠላሳ በርሜል
በዚህ ጊዜ ፊታውራሪ ገበየሁ በወደቁ ጊዜ በጅሮንድ ባልቻ ኃላፊነቱን መወጣት በመቻላቸው
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ
ተብሎላቸዋል። የስንኙ ሐሳብ ውስጥ ሞት አለ። በዚያ የሞት መርዶ ውስጥ ግን ሙሾ ላይ እንደተመለከትነው ያለ ሐዘን የለም። ግጥሙ ያለፈን የመተረክ፣ ትላንትን የማስታወስ አዝማሚያው ያመዝናል።
ተክለጻዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው ጥራዛቸው ካሰፈሩት አንድ እንጥቀስ
ሰባት ደጃዝማች አስር ፊታውራሪ የጠመቀውን
የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን
ወሌ በጉሎ ዘሎ ቢወጣ
ይመስላል ሐምሌ ክረምት የመጣ
የሚሉት መወድስ ስንኞች ይገኛሉ። የቴጌ ጣይቱ ብጡል ወንድም ራስ ወሌ ብጡልን ያወደሰው የአዝማሪ ስንኝ ለዛሬው አድማጭ ታሪክ ነጋሪ ሰበዝ ያቀብለዋል።
ቀኛዝማች ባሻሕ ለተባሉት አንድ ዐይና አርበኛ የተገጠመው የአዝማሪ ግጥም ጀግንነታቸውን ብቻ ሳይሆን የሰውነት አቋማቸውንም የሚያስነብብ ነው።
አፉ ጎራዴ የለው አሽሟጣጭ
ባሹ አባ ሳንጃ በአንድ ዐይኑ አፍጣጭ
ተክለጻዲቅ መኩሪያ “ከአጼ ታድሮስ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ” በተሰኘው ድርሳናቸው ካሰፈሩት የአዝማሪ ውዳሴ ደግሞ ተከታዩን እንውሰድ
አባተ በመድፉ ኃምሳውን ሲገድል
ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል
የጎጃሙ ንጉሥ ግፋ በለው ሲል
እቴጌ ጣይቱ እቴጌ ብርሃን
ዳዊቷን ዘርግታ ስምአኒ ስትል
ለቆሰለው ጀግና ውሃ ስታድል
እንዲህ ተሰርቶ ነው የዓድዋ ድል
ጥልያን ኮሶ ጭኖ ሸዋን ሊያጠጣው
ገና ሲበጠበጥ ዳኘውን ቀናው
ቅዳሜ ተጉዞ እሁድ ተበራየ
መስኮብም ገረመው ጣልያንም ጉድ አየ
አገርክን ምኒልክ እንዳሁን ፈትሻት
ባያይህ ነውና ጠላትህ የሚሻት
እጁን ቀምሼ አላውቅ እያለ ሲማህ
ቀመሰና እጅህን መጥቶ ጠላትህ
ሮም ላይ ተሰማ ለጋስ መሆንህፓ
ጳውሎስ ኞኞ ጆርጅ በርክሊን ጠቅሶ ለፊት አውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) ከተበረከቱ ውዳሴዎች ውስጥ ይህንን አስነብቧል።
የንጉሥ ፊታውራሪ የጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም አልበቁት ቁርስ አደረጋቸው።
የአምባላጌው ጦርነት ላይ ከገበየው ሌላ ትልቅ ጀብዱ የፈጸሙት ጀግና ፊታውራሪ አባ ውርጂ ነበሩ። እርሳቸው በጦርነቱ ላይ ማጆር ቲዚሌ–ን ብቻውን አገኙት እርሱ ጦሩን ከፍ ብሎ በመቃኘት ላይ ባለበት ጊዜ ድንገት ተገጣጠሙ። ሽጉጡን የማውጣት ፋታ እንኳን ሳይሰጡት ዘለው ተጠመጠሙበት። ትግል ገጠሙት። እንደተናነቁ ወደ ገደል ጫፍ ደረሱ። ገደል ሊወረውሩት መሆኑን የተረዳው ማጆር የሞት ሞቱን እሳቸውንም ይዟቸው ገባ። ተያይዘው ገደል ውስጥ ገቡ።
ይህንን ታሪክ ሳይሰማ ማጆር መሞቱን ብቻ የሰማው አዝማሪ እንዲህ ገጠመ።
አላጌ እበሩ ላይ ሲወድቅ ማጆር
እንደ ግራኝ ሁሉ በሰባት አረር
ያንን ያህል ታላቅ የጦር ሰው በቀላል ሊሞት አይችልም የሚለው የአዝማሪው ግምት ስህተት ነበር። በኋላ ላይ ዋናው ታሪክ የተሰማ ጊዜ ተሳቀበት። ለእውነተኛው ገጠመኝ የተስማማውን ግጥም ደግሞ ሌላኛው አዝማሪ እንዲህ አስተላልፎልናል።
ጀነራሉን ማጆር ቶዚሊ
ማን ይነካዋል ያለ ፈጣሪ
ገደል ሰደደው አንድ ፊታውራሪ
ለበጅሮንድ ባልቻ ሳፎ ወይም ባልቻ አባ ነፍሶ ከተገጠሙት ግጥሞች መካከል ደግሞ ተከታዮቹ ይገኙበታል።
አሻግሮ ገዳይ ዲብ አንተርሶ
የዳኘው አሽር ባልቻ አባ ነፍሶ
እንደ ደጋ ገብስ እንዲያ ኮስሶ
ያስቆረጥማል ጠላቱን ኮሶ
የዳኘው ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ