መልክን የሻሩ ዘፈኖች
በዳዊት አርአያ
የበዛ ቁጥር ያላቸው ዘፈች እና ዘፋኞቻችን ዋና ርዕሰ ጉዳይ ፍቅር ነው። ከፍቅርም የተቃራኒ ጾታ ፍቅር፣ በመውደድ መጥላት፣ በመቅናት ማስቀናት፣ በፍቅር ስቃይ፣ በልንገር አልንገር ውዝግብ፣ በናፍቆት፣ በመክዳት መከዳት፣… ላይ ያተኮረ ፍቅር። ውበት፣ ደምግባት፣ ርዝመት (የአንገት፣ የቁመት፣ የእጅ ጣት)፣ ዐይን፣ ጥርስ፣ ደረት፣ ጸጉር፣… ሁሉም ተዘፍኖላቸዋል። መልከ-መልካምን ሴት አሞግሰዋል። በሕይወት ባህር ላይ ግን መልከ መልካም ሴት ብቻ የለችም። ዓለም የመልከ ጥፉዎችም ነች። ውበት እንደተመልካቹ ቢሆንም፣ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር እንዳለው ሁሏም ሴት ላይ ለወንድ ውበት ቢቀመጥለትም፤ ‘በዘፋኞቻችን ጉሮሮ ተደጋግሞ የሚቀነቀነው ‘ፍቅር’ ከደምግባት ጋር ብቻ ተሳስሮ ሲኖር ታዝበው ‘ሌላም መንገድ አለ!’ ብለው የታደጉትን አበጃችሁ ልንል ነው። በአያሌ ዘፈኖቻችን ውስጥ ለዘመናት የተጓዘበትን መንገድ ጥለው ውበትን ከፍቅር ነጥለው ያሳዩንን ዘፈኖች ልንመለከት ነው። ፍቅር ያስውባል፣ ፍቅር ከአካላዊ ውበት በላይ ነው። ያሉንን የዘፈን ስንኞች ልንዘርዝር…
ሚስትህ በጣም ፉንጋ ናት- ፉንጋ ከኔ የባሰች
አንተን መሳይ አደላት- ቀድማ ስላልፈረደች
አንተ በጣም ቆንጆ ነህ- በሚያነጋግር ዐይነት
በውነት ግራ ይገባል- አንተን ከሷጋር ማየት
/ዘሪቱ ከበደ/
ዘሪቱ ከበደ ከውብ ድምፅ እና የአዜያዚያም ዘይቤ በተጨማሪ የተባ ብእር የታደለች የግጥምና ዜማ ደራሲ ነች። የምታዘጋጃቸው የግጥም እና ዜማ ድርሰቶች ግሩም ናቸው። በግሌ የአቅሟን ያህል እየሰራች ነው ብዬ ባላምንም በሰጠችን አንድ አልበም እና ነጠላ ዜማዎቿ የተካተቱት የግጥም ሀሳቦች ከፊሎቹ ከዚህ ቀደም በዘፈን ያልተነሱ፤ ገሚሶቹ እንደምን ስትል ይህን ሀሳብ፣ ይህን ገለጻ ለዘፈን ተጠቀመች የሚያስብሉ፤ የተቀሩት ደግሞ ከዚህ በፊት ብዙ የተባለባቸውን ከማለት በላይ በሆነ በራሷ ገለፃ የተራቀቀችባቸው ናቸው።
በነጠላ ዜማነት የሰማነው “የወንድ ቆንጆ” የተባለው የግጥም ሀሳብ ከላይ ከዘረዘርነው ‘በዘፈን ያልተነሱ’ ሀሳቦች መሀከል ልንመድበው የምንችል አስገራሚ ሀሳብ ያዘለ ዘፈን ነው።
በግጥሙ ውስጥ 3 ባለታሪኮች ተስለዋል። 2 ሴት እና 1 ወንድ። ሁለት ፉንጋ ሴቶች እና አንድ ቆንጆ ወንድ። ተራኪዋ ሴት ናት። ፉንጋ መሆኗን የምታውቅ፤ የመልኳን ደረጃ ተረድታ ሰውን በመልኩ የምትሰፍር፤ መጽሐፍን በሽፋኑ የምትመዝን አላዋቂ… ፍቅርን ብሎ ፍቅርን ሽቶ “ይህ አለኝ! ይህ የላትም” ሳይል የቀረባትን ወንድ ማኅበረሰቡ ባሳደረባት የአስተሳሰብ ተጽእኖ ምክንያት “ወግድልኝ!” ለማለት የምትደፍር የዋህ።
ወደኋላ መለሰኝ- አሳሰበኝ ስለኛ
የጀማመርከኝ- ሰሞን እንድሆንህ ፍቅረኛ
ቆንጆ ወንድ ማፍቀር ትርፉ- እርም ብዬ መከራ
ግዴን ተከላክዬህ- ኮራሁብህ ሳትኮራ
ልቤ ፈራ ፈራ
እያለች የምታንጎራጉር… ተወኝ ስትለው ትቷት፣ ሂድልኝ ስትለው ሰምቶ ከአጠገቧ ርቆ ሄዋኑን ያገኘ፤ የቀድሞ አፍቃሪዋ አገባ። ሴቲቱ በባለትዳሩ የቀድሞ አፍቃሪዋ እንድትቀና፣ ትላንቷን እንድትመለከት ያደረጋት የሚስቱ ፉንጋነት ነው። ከሷ የባሰች ፉንጋ መሆኗ። “ደግሞ የወንድ ቆንጆ” የሚለው ስሁት ድምዳሜዋ!
እሷግን አመነችህ- ትንሽነት ሳይሰማት
ፉንጋ ሳለች ስታምርህ- ተማምና እንደምትገባት
ትለዋለች። እኔ መልክ ዓይቼ ስመለስ፣ ውስጥህን ሳላይ ስሳሳት፣ በኖረ ልማድ ስወሰድ፣ ደግሞ የወንድ ቆንጆ በሚሉት ብሂል ስታለል እሷ ግን… ትልላታለች።
ሲባል እማውቀው- ልቤም ሲፈራ
እንዳልጎዳ ብዬ- አንተም እንዳትኮራ
ልቤ ፈራ ፈራ
*
ቆንጆ ወንድ ማፍቀር ትርፉ- እርም ብዬ መከራ
ግዴን ተከላክዬህ- ኮራሁብህ ሳትኮራ
በውብ ስንኞች የተገነባው የዘፈን ግጥም የሚጠናቀቀው ፉንጋ ተብላ ስትገለጽ የነረችውን እንስት ቆንጆ በማለት ነው። ዘሪቱ በግጥሟ ይህንን ያደረገችው በስህተት አይደለም። ሆን ብላ ነው። ተራኪዋ ገጸ-ባህሪ /እኔ ባይ ተራኪ- ስህተቷን ስትረዳ፣ ፍቅርን በመልክ ሚዛን መስፈሯን ስትተው ሸውራራ ዕይታዋ ይታረቃል። ያኔ ከደምግባት በላይ ማሰብ ትጀምራለች። ፉንጋነት ይምታታባታል። “ኧረ እርስዋም ቆንጆ ናት” ትላታለች።
ሎጋ ለሎጋ
ሲያወጋ ነጋ
ቆንጆ ለቆንጆ
ይሰራል ጎጆ…
መባልን ሲሰማ ላደገ የሚጎረብጥ ሀሳብ ቢመስልም፤ ከእውነታው ሲናጸር ግን ሁልጊዜ አይሰምርም።
ቀጣይ ማረፊያችን ኢዮብ መኮንን ነው። /ነፍስ ይማር/ “እንደቃል” የተሰኘ መጀመሪያ አልበሙ ውስጥ የተካተተው እና ኤሊያስ መልካ ጽፎ ያቀናበረው “ደብዝዘሽ”
ኤልያስ ድምፅ ጩኸት ነው። ድምቀት መብለጭለጭ ነው። ደስታ ሳቅ ብቻ ነው። ባዮችን የመከተበት ሌላም መንገድ አለ ያለበት ዘፈን ነው ደብዝዘሽ። ልብ ባንልም- የምንኖረውን እውነታ የገለጠ
መልክን የሻረ
አንቺጋ ምን ተሻለ
ከሩቅ ሳትስቢ
ዓየሁ ልቤ ስትገቢ…
ብሎ ይጀምራል።
ካንቺ በላይ ቆንጆ ሞልቶ
ያውቃል ልቤ ቀርቦም አይቶ
ግን በምን በለጥሻቸው?
ቆንጆዎቹን አስናቅሻቸው?
ደብዝዘሽ አጋለጥሻቸው?…
ብሎም ይጠይቃል። ይህች የሚዜምላት ሴት ማኅበረሰቡ ባስቀመጠው የቁንጅና ደረጃ ከፊት የለችም። ከሩቅ አትስብም።
ዓይነ ኮሎ- ሽንጠ ሎጋ የወለዱ እንደሆን
ታመጣለች አማች ብረት መዝጊያ እሚሆን…
የሚባልላት አይደለችም። ወንዱን ሁሉ በውበቷ አንበርክካ የኔነች የአንተ አይደለችም በሚል ዱላ አላማዘዘችም።
ከአንቺ በላይ ውበታቸው
ከአቺ በላይ ዕውቀታቸው
ስቄም ነበር በቀልዳቸው
ግን በምን በለጥሻቸው ?…
የሚባልላት አይደለችም። ወንዱን ሁሉ በውበቷ አንበርክካ የኔነች የአንተ አይደለችም በሚል ዱላ አላማዘዘችም።
ከአንቺ በላይ ውበታቸው
ከአቺ በላይ ዕውቀታቸው
ስቄም ነበር በቀልዳቸው
ግን በምን በለጥሻቸው ?…
ይህ ሁሉ ቢሆንም ከልብ ትገባለች። ይባስ ብላ የልኬት ጣራ ትሆናለች። “አንቺን ካልተስተካከለች የታል ቁንጅናዋ?” ታስብላለች። መልከ-መልካምነትን ታስረሳለች።
ምንድነው ብርቅ ሆኖ የሚያስወድደኝ
ሁሉሽን እንዳደንቅ የሚያስገድደኝ
ቆንጆም ውብም ለእኔ የአንቺ ዓይነት ብቻ
ባይም ልቤ አያምንም እንዳለሽ አቻ…
ይባልላታል። ቦታ ሲለዋወጡ ታዘባችሁልኝ? በአእላፍ ዘፈኖቻችን እንዳደመጥነው በዚህ ዘፈን ውስጥ ያለውን ፍቅር መልክ አልወለደውም። አፍዞ የሚያስቀር ቁንጅና አይደለም ገጣሚን ነሽጦ ብእር ያስጨበጠው። ደብዛዛ ውበት ነው አንጂ፤
አንዲት ስሟ የተዘነጋኝ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች በአንድ ቃለ-መጠይቋ እንዲህ ብላ እንደነበር መስማቴን አልዘነጋሁም።
“በርካታ ሰዎች ከሜዳ ውጪ ሲያገኙኝ ስለችሎታዬ ሳይሆን ስለ ቁንጅናዬ ይነግሩኛል። እኔ የምፈለወገው ግን ስራዬን እንዲያስበልጡልኝ ነው።”
ነገሩ ቅብጠት ይመስል ይሆናል። በባለቤቱ ጫማ ላይ ሆኖ ሲታይ ግን ህመሙ ይጠልቃል። ለፍተው ጥረው ካመጡት፣ መሆን እና ማድረግ ከሚፈልጉት ነገር በላይ- ለመኖሩ ምንም አስተዋጽኦ ባላደረጉበት ነገር መጠራት፣ ሙሉ ምስጋናውን ተፈጥሮ ብቻ በምትወስደው፣ ምንም ባልጣረችለት ስጦታ መመስገን፣ በታደሉት እንጂ ባልታገሉለት መሞገስ…
ቢደምቅም ባይደምቅም- ቢበርደው ቢሞቀው
ላይሽ ብቻ አይደለም ልቤን የደነቀው
መች ዐይኔስ ሆነና ከላይ ዓይቶሽ ብቻ
መች ድሮስ ሆነና ካንገት በላይ ምርጫ
ልቤ አንቺን እንጂ መች መልክሽን ብቻ
መች ዓየ እሱን ብቻ
የሚለው የጌቴ አንለይ ዘፈን በመድኃኒትነት የሚከሰተው ይህን ጊዜ ነው። “መልክሽ አይበልጥሽም” ከሚል ዘፈኑ ላይ። ይህ የመጨረሻ አልበሙ በግጥም ረገድ ጥሩ ጥሩ ሀሳቦችን ያነሳበት፣ ከተለመደበት አዘፋፈን የወጡ ስልቶችን የሞከረበት ድንቅ ሥራው ነው።
ለመልኳ ምንም የማይወጣላት ገጸ-ባህሪ እዚህ ዘፈን ውስጥ አለች። ልቅም ካለው መልኳ በላይ በእሷነቷ፤ መርጣ ባመጣችው ማንነቷ፤ ሊመዝናት የሚሻ አፍቃሪዋ እንዲህ ያንጎራጉርላታል።
መች እተውሽ ነበር ዐይኔ እስኪያይሽ ድሮ
ባይኖር እንኳን መልክሽ ውብ ባትሆኚም ኖሮ
ከላይ ዕዩኝ ባለች ባደባባይቷ
አንቺ አትመዘኚም በብልጭልጪቷ
ውብ ቢሆን በርግጥም
መልክሽ ከአንቺ አይበልጥም
ምን ቢሆን ከውጪ አንቺ አትለወጪም።
እያለ ከመልክ ውጪ ያለ ማንነት እንደሚያፈዝ፣ በውበት መዝገበ ቃላት ላይም እንዳለ እና እንደነበረ፣ ይነግረናል። በጌቴ አንለይ ስርቅርቅ ድምጽ እየተዋዛ አስተሳሰባችንን ይቃኛል።
ለኔ አዲስ ነሽ ውዴ
በጄ እስክትገቢልኝ- እስከሚያቅፍሽ ክንዴ
አይደለም መውደዴ…
እያለ ከጊዜያዊ ሙቀት በላይ ያደገውን የፍቅሩን መግለጫ ያቀርባል። ይህ ብቻ አይበቃውም ውስጣችን የኖረውን የውበት ብያኔ ሊያፈራርሰው ይጥራል።
ጊዜ ሲለዋወጥ ወራቱ ሲጨምር
ይነጥፍ የለም ወይ ውበት ቢሆን ጸጉር
እንኳን ሲበስልና የድሮ ቀን ሲከብደው
መልክማ ይቀየራል ላንዳፍታም ቢበርደው
ላዩማ ኃላፊ ነው መልክና ደም ግባት
ሁሌም ግን አያልፍም ብርቅ የልብሽ ውበት
የጥላሁን ገሰሰ እና የብዙነሽ በቀለ ቆየት ያለ “እሺ በይ” የተሰኘ የቅብብል ዜማ እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለት ነው።
አቤት ዓይንሽ አቤት ጥርስሽ ውበቱ
ልብ ይሰውራል ልዩ ነው ፍጥረቱ
ልብሽ ጨካኝ ነው መቼም አይበገር
ኧረ አንቺ ልጅ ወይ ብትይኝ ምን ነበር…
እያለ ለዛ ባለው ዜማ ሲያዋያት እንዲህ ስትል ትመልስለታለች።
ስለዓይኖቼና ጥርሶቼ ቁንጅና
አትጨነቅ የአምላክ ሥራ ነውና
መለወጥ በምችለው፣ ፈልጌ ባለጣሁት ነገር ላይ እንነጋገር የሚል ዓይነት ስሜት አለው። ያምላክ ስራ ነው የኔ እጅ የለበትም።
ሌላው ተጠቃሽ ሰይፉ ዮሐንስ ነው። የዘፈኑ ርእስ “እመቤትነትሽ” ይሰኛል። የአክብሮቴ ሚዛን የሚለካው፣ የፍቅሬ ጥልቀት የሚመተረው፣ አድናቆቴ የሚመነጨው በመልክ መስፈሪያ አይደለም። በዝና ሜትር አይደለም። ይለናል በስንኞቹ- እነሆ የስንኙ ድርድር
በመልክሽ አይደለም ውበትሽን የማውቀው
በዝናሽ አይደለም ስምሽን የማደንቀው
በጨዋነትሽ ነው በእውነተኛነትሽ
ያንቺ ትልቅነት እመቤትነትሽ
አስቴር አወቀም ያነሳነውን ርዕሰ-ጉዳይ የተመለከተ ዘፈን በውብ ለስላሳ ድምጿ አቀንቅናለች። እንዲህ ስትል…
ከሁሉም ከሁሉም ጎልቶ የሚታየኝ
ዘወትር እንድወድህ የሚያስገድደኝ
አይደለም ገንዘብህ ወይም ውበትህ
ግሩም ጸባይህ ነው የእኔ ያረገህ
ዳዊት መለሰ ደግሞ፡-
አፍንጫ ምን ቢቆም ቢገተር
በረዶ ጥርስ ቢደረደር
ተረከዝ ባትና ቁመና
መች ዓይቶ ልቤ ፈለገና
ለውበት አይሳሳም ገላዬ
ዘወትር አንቺነሽ ምርጫዬ
ስል አዚሟል።
ለመሰናበቻ ታምራት ሞላ ካቀነቀነው ሙዚቃ አንድ መንቶ እናንሳ
መልኳ መጠነኛ ቁመቷም አጭር ነው
የተዋደድንበት ነገሩ ሌላ ነው