ሄኖክ መሃሪ ልዩ ድምፁን እና ምርጥ ስራውን በአለምአቀፍ ደረጃ ለመቀጠል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ፕላትፎርም ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር ተፈራረመ።
“ሙዚቃ ለእኔ ከእውነተኛ ስሜቴ እና ከአድናቂዎቼ ጋር የምገናኝበት፣ ለኪነ ጥበብ ታማኝ መሆንን የተማርኩበት መንገድ ነው።”
– ሄኖክ መሃሪ
የቀድሞ ህይወት
ሄኖክ መሃሪ በ2006 የተመሰረተው የመሃሪ ብራዘርስ ባንድ ተባባሪ መስራች ፣ፒያኒስት እና መሪ አቀንቃኝ ሲሆን ተወልዶ ያደገው ከአባቱ መሀሪ አብርሃ (ዘማሪ፣ ዜማ ደራሲ እና ሳክፎኒስት) እና እናቱ አጼነሽ አበበ (ዳንሰኛ፣ ኬሪኦግራፈር) በአዲስ አበባ አራዳ ክ/ከተማ በተለምዶ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
በሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ለመግባት ያነሳሳው የወንጌል መዘምራን አካል ከሆነ በኋላ ሲሆን አብዛኛውን የወጣትነት ህይወቱን የቀረፀው እዛ ነው። ከዚያም የወላጆቹን ፈለግ በመከተል ህልሙ ወደ ሙዚቃ ማዘንበል ጀመረ።
ሄኖክ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በራስ አበበ አረጋይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በእንጦጦ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን በአዲስ አበባ የኪነጥበብ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱን አጠናቋል። በትወና፣በጽሁፍ እና ፊልሞችን እና የሙዚቃ ቪዲዮዎችን እንዲሁም የህይወት ታሪኮቹን በማተም የትርፍ ጊዜውን የሚያሳልፍ ሲሆን አሁን ላይ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነው።
የሙዚቃ ህይወት
አርቲስት ሄኖክ መሃሪ በሸራተን ጋዝላይት ቡፌ ደ ላጋር ላይ የመጀመሪያውን ትርኢት ያሳየ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2006 ከወንድሞቹ ጋር መሃሪ ብራዘርስ ባንድ በመፍጠር የአባቱን ህልም አሳክተዋል። ። ባንዱ በዲሲፕሊን፣ በአንድነት እና በልዩ መንገድ ጠንካራ ስም ያለው ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ጋር ትርኢት አሳይቷል። የመጀመርያው አልበሙ “እውነተኛ ፍቅር” የሚል ርዕስ ነበረው ።
ይህን አልበም ያዘጋጀበት ምክንያት ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ ፒያኖ መግዣ ገቢ ለማግኘት የነበረ ሲሆን ባሰበውም ልክ ለማሳካት ችሏል። ወደ ሁለት አስርት ዓመታት ከሚጠጋ የሙዚቃ ስራ በኋላ፣ በመላው አፍሪካ፣ አውሮፓ እና ምዕራብ ሃገራት ባሉ ግዙፍ የሙዚቃ ጉብኝቶችን አላማ አድርጓል።
ሄኖክ ለብዙ አመታት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የቲቪ እና የሬዲዮ የንግድ ሙዚቃ ፕሮዳክሽኖችን፣ፈጠራ አጋር ፣ ድንቅ የዘፈን ደራሲ እና የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር በመሆን የሰራ ሲሆን ከዚም በተጨማሪ እንደእዳይገለኝ ለዘሪቱ ከበደ ፣ቼዋታ ለወንዲሙ ጅራ ፣ምርጫዬ ለፀደንያ ፣ዕድሜየን በሙሉ ለአብርሽ ዘጌት እና ሌሎችም ተወዳጅ ዘፈኖችን በመፃፍ እና በማዘጋጀት ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር በመስራት ታዋቂነትን አጊኝቷል።
እድሎች
በአልበሙ ምክንያት ሄኖክ መሃሪ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ብዙ እድሎችን አግኝቷል። በጁላይ 2016 ሄኖክ በኮክ ስቱዲዮ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለአንድ ሳምንት የቪዲዮ እና የድምጽ ቅጂ ተጋብዞ የነበረ ሲሆን የእሱ አፈጻጸም በጣም ከፍተኛ ደረጃ ያለው በመሆኑ ኮክ ስቱዲዮ ከዘፈኖቹ ውስጥ አንዱን ‘ሆያ ሆዬ‘ ለመላው አህጉር የማስተዋወቂያ ቪዲዮ አድርጎ ይጠቀም ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሄኖክ መሃሪ 790 አልበሙን አውጥቶ በዓለም ዙሪያ ካሉ አድናቂዎች ትልቅ ምላሽ አግኝቷል ።
ሚውዚኮሎጂ
ሔኖክ ላለፉት ሶስት አመታት በቃና አሁን ደግሞ በዲኤስቲቪ አቦል ቲቪ ላይ ሲሰራ የቆየው ቶክ ሾው ፅንሰ–ሀሳብ ሙዚቃ እና ቶክ ሾው የሚል ሳምንታዊ የቴሌቭዥን ሾው ይዞ መጥቷል። ይህ የቴሌቭዥን ቶክ ሾው ከጀመረ ላለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ ባሉት ውብ የቀጥታ ትርኢቶች እና ሁለገብነት፣ ምሁራዊ እይታ እና ፍልስፍና ከሌሎች ሙዚቀኞች እና ከሙዚቃ አድናቂዎች ትልቅ ክብርን አትርፏል።
ሽልማቶች እና እጩዎች
ከዚህም በተጨማሪ ሄኖክ መሃሪ በአፍሪካ ምርጥ አር ኤንድ ቢ ሶል ባንድ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለ All African Music Awards (AFRIMA) በመመረጥ በኢትዮጵያ ትልቅ ሪከርድ ሰብሯል። እስካሁን በአህጉር ደረጃ በእጩነት የተመረጠ እና ያሸነፈ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ወንድ አርቲስትም ነው።
እ.ኤ.አ. ህዳር 5 ቀን 2016 ሄኖክ እና ወንድሞቹ ሽልማት ይዘው ከናይጄሪያ ሌጎስ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት መላውን ኢትዮጵያ አኩርተው እሱም በድጋሚ እጩ ሆኖ ነበር።
እ.ኤ.አ. በ 2017 በሁለት ምድቦች ማለትም የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ወንድ አርቲስት በክልል ምድብ እና በምርጥ ሬጌ ራጋ በአህጉራዊ ምድብ እንዲሁም የዳንስ አዳራሽ አርቲስት ቡድን ምርጫ ውስጥ ቀርቦ ነበር። እ.ኤ.አ. ኦገስት 2017 ከወንድሞቹ እና ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በስፔን የሮቶቶም ሰንስፕላሽ ሬጌ ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በመወከል ትርኢት አቅርቧል።
ከሰዋሰው ጋር
ሄኖክ አድናቂዎቹ እና ተከታዮቹ ጋር ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር የተፈራረመ ሲሆን የእሱን ፈለግ መከተል ለሚፈልጉ ሁሉ “…የእኔን ፈለግ ለመከተል ለሚፈልግ ሰው የምመክረው የእኔን ፈለግ ከልክ በላይ አትከተል፣የራስህን ፈለግ እና ማንነት ፍጠር፣በተቻለ መጠን እውነተኛ ማንነትህን ኣግኝ፣ ለራስህ እና ለጥበብህ ታማኝ ለመሆን ሞክር እናም ገንቢ ካልሆነ በስተቀር ከተቺዎች ማንኛውንም አላስፈላጊ ምክር አትስማ…” ሲል መልክቱን አስተላልፏል።
በቅርቡ…