ከሁዳዴ እስከ ትንሳኤ:
በኪነ-ጥበብ ሥራዎች ውስጥ
በዳዊት አርአያ
የዘፈን ግጥሞቻችን ከሚያጠነጥኑባቸው ሐሳቦች መካከል ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ በዓላት ይገኙበታል። ዘፈኖቹ የእንኳን አደረሳችሁ ይዘት ያላቸው ወይም የተቀሰቀሰ ትዝታን የሚያስታምሙ ሊሆኑ ይችላሉ። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የትንሳኤ በዓልም በበርካቶች ከተዜመላቸው በዓላት መካከል ተጠቃሽ ነው። የ55 ቀናት ርዝማኔ ያለው ሁዳዴ በስነ-ጽሑፍ እና ሙዚቃ ሥራዎች እንዴት እንደተገለጸ በዚህ ጽሑፍ ለመመልከት እንሞክራለን።
የዘንባባው ቀለበቴ
ይሁን ከጣቴ
በቀና ልብ ያጠለቅነው የልጅነቴ
የቤቲ ጂ የዘንባባ ቀለበቴ ወደ ልጅነቷ የተመለሰችን ገጸ ባህርይ ሕመም ይተርካል። የትንሳኤ በዓል ጅማሮ የሆነውን የሆሳእና በዓል ታሪካዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊ ሁናቴ የመተረክ ዓላማ የለውም። በዘንባባው ቀለበት ጎታችነት ወደ ህጻንነት ዘመን የተጓዘችን እንስት ትዝታ ያስቃኛል። የጮርቃነት ፍቅሯን ታነሳሳበታለች፡፡ መሰረቱ ሀይማኖታዊ ቢሆንም ሰብአዊ ገጠመኝም አያጣምና ያንን ሰብአዊ ጉዞ ለማንሳት የሞከረ ዘፈን ነው፡፡
እኔስ ተመኘው ያንን ዘመን
የልጅነቴን ሙሽርነቴን
እያለች የእለተ ሆሳእናን ትዝታ ታመነዥጋለች፡፡ በርካታ ዓመታት ቢያልፉም የጸና ንፁህ እምነት ያለበትን እውነተኛ የልጅነት ሕይወት በወጣትነት ጎዳና በምትጓዝ እንስት ገጸ-ባህርይ አማካኝነት እናደምጣለን፡፡ የዘንባባው ቀለበቴ…ሁዳዴ በዘፈን ውስጥ የተገለጠበትን አውድ ስንመረምር በርካታ ዘፈኖች ታጋሽነትን ገልጸውበታል። ርዝመቱን፣ በወቅቱ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የማይፈቀዱትን ተግባራት አስበው ችኮላን ነቅፈውበታል።
በጾመ ሁዳዴ ጾም በተያዘበት
ይቺ ሰው ገደፈች በላች የሰው አንጀት
ሙሉቀን መለሰ ደግሞ አንጀት የምትበላዋን ሴት አንስቷል። ቅኔያዊ አገላለጽ ያለው የዘፈኑ መንቶ ከላይ ያነሳነውን አካሄድ ይጋራል። ለዓለማዊ ክዋኔ ገለጻ ሁዳዴን ተጠቅሟል። በተመሳሳይ የገለጻ ብልሃት ስንኞቻቸውን የገነቡ ዘፈኖች በርካታ ናቸው።
ሁዳድነቱን መሰረት ያደረጉት ስንኞች ሀይማኖታዊ መልእክት የላቸውም። የስንኝ ድርድሮቻቸው መልእክት መንፈሳዊውን ግልጋሎት የታከከ ይሁን እንጂ ዓለማዊ ነው። እማሬያዊ ፍቺውን የተንተራሰ ነው። ‘የማነሽ ይሉኛል’ በተሰኘው የበዛወርቅ አስፋው ዘፈንም የምናገኘው ይህንኑ ነው። ‘‘አቻሽ ማን ነው?’’ የሚል ጥያቄ ያታከታት እንስት ገጸ-ባህርይ የተናገረችው ነው። ‘‘ሁዳዴን እንኳን እንታገስ የለም እንዴ? ካስቻለኝ ብታገስ ምኑ ነው ነውሩ?’’ ትላለች። በግሩም ድምጿ፣ በልከኛ ግጥም እና ዜማ… በዛወርቅ አስፋው
መጾም መታገሱን ከቻለልኝ ሆዴ
ይከረም የለም ወይ ሁለት ወር ሁዳዴ
ወተት ወተት ይላል ፍቅር የያዘው
ሁለት ወር ሁዳዴን እንደምን ጾመው
ይህ የአስቴር አወቀ ዘፈንም መንታ ፍቺ እንዲሆረው ሆኖ ተሰናድቷል። በፍቅር ሕመም ውስጥ የሚገኝን ሰው ሁናቴ እና በጾም ወቅት ያለን ስርአት አጣምሮ ያወሳል።
የከረረው ድምጹ ቢያሳዝነው ሆዴ
ትእዛዛቱን ፈራሁ ጾም ሁኖ ሁዳዴ (ብዙአየሁ ደምሴ)
ለምሳሌ ያህል ማሳያ ቢሆኑን ብለን እነዚህን አነሳን እንጂ ሁዳዴን በማንሳት መልእክታቸውን ያጠናከሩ፣ ለዘይቤ ማሳመሪያነት የተጠቀሙ በርካታ ናቸው።
የሁዳዴ እያንዳንዱ ሳምንት የግሉ ስያሜ አለው። ስያሜ ብቻ ሳይሆን ትርጓሜ፣ ምሳሌ እና ታሪክም ጭምር አለው። ዘወረደ ብሎ ጀምሮ ትንሳኤ እስከሚል ድረስ ምስጢራዊነትን ያዘለ ልዩ ስያሜ ታድሏል፡፡ ቀደም ሲል ሆሳእናን መሰረት ያደረጉትን እንዳነሳን ሁሉ መጻጉእን ያነሱ የጥበብ ሥራዎች አጋጥመዋል። የይሁዳን ያህል ባይሆንም በአብዛኞቹ ላይ ዓለማዊ ይዘት ያላቸው ሥራዎች አጋጥመዋል። የይሁዳን ያህል የኪነ-ጥበብ ከዋኞችን ቀልብ የሳበ የለም ብሎ ማለት ደፋር አያስብልም። በበርካታ መድረኮች ላይ ይሁዳን የሚነቅፉ፣ የሚያወድሱ፣ አልተሳሳተም፣ ባለ ውለታ ነው፣… የሚሉ መነባንቦች አድምጠናል። ታምራት ደስታም ‘እንደ ይሁዳ’ ሲል ዘፍኗል።
ምነው በጾም በጸሎት ሲሻው ሃገር
ገፋሽ ፍቅርን የሚያህል ንጹህ ነገር
በዘፈኑ የተገለጹ ገጸ ባህርያትን ውጣ ውረድ ከኢየሱስ የምድር ጉዞ ጋር በማዛመድ የሚከወን የጥበብ ዘውግ አለ። ‘ምስለ-ኢየሱስ’ ይሰኛል። የዘፈን ግጥሙ አካሄድ በዚህ ዘውግ የተሰራ ይመስላል። ኢየሱስ ለፍቅር ራሱን ሰጥቷልና ፍቅር የሚል ተጸውኦ አለው። ፍቅርን በጾም በጸሎት ይፈልጉታል የሚለው ሃረግ የጾምን ትርጉም ያመሰጥራል። ምንም እንኳን ዓለማዊ መልእክት ቢኖረውም ለምስለ-ኢየሱስ የቀረበ የአሰነኛኘት አካሄድ አለው።
ክህደትሽ አሳልፎ ለሐዘን ከሰጠኝ
ለኔስ ይሁዳ ነሽ ሌላ ቃልም የለኝ
ይሁዳዊ ተግባር ፈጽማብኛለች ያለ ተበዳይ ነው። አጻጻፉ ለምስለ-ኢየሱስ ይቀርባል ለማለት የሚያስደፍረውም ቀና ውሳኔን ሲወስን ስናደምጥ ነው።
እንኳን ቀረ በዚሁ ደግሞ ለሌላ ሐጥያት
ከምትሰጫት ለበቀል የልቤን ከረጢት
እንዲህ እንዲህ እያለ የሚቀጥለው ዘፈን የይሁዳን ታሪክ ለራሱ ዓላማ ተጠቅሞበታል።
የኤፍሬም ስዩም የይሁዳ ድልድይ እዚህ ላይ መነሳት የሚችል ነው። የይሁዳ ድልድይ እና ሌሎች ሃሳቦች በሚለው ሥራው ወስጥ ተካቷል።
‘‘እናንተ ከምታውቁት በላይ መሲሁን በአካልም በመንፈስም አውቀዋለሁ። በቃሉ ታማኝ እና ንጹህ፣ ያለማዳላትም ፍጥረቱን በእኩልነት የሚመለከት ቢኖር መሲሁ ብቻ ነው። ለዚህ ምስክሩም ከዋለበት የምውል፣ ካደረበት የማድር ከሌሎች ምስክሮች የምለይ፣ እኔ ይሁዳ ብቻ ነኝ። እኔ እንደሌሎቹ ጓደኞቼ ስለሱ መልካምነት ለመመስከር ስደት እና ረሃብ፣ እስራት እና ስቃይ አያስፈልገኝም። እንዲያውም ባልንጀሮቼ ከተቀበሉት መከራና ስቃይ የኔ ይልቃል’’ የይሁዳ ድልድይ ገጽ 201
የሚለው እኔ ባይ ገጸ ባህርይ በይሁዳ በኩል ያሉትን እውነቶች እያነሳ እምነታችንን ይፈትናል።
ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ‘ከጥቁር ሰማይ ስር’ በተሰኘ የአጫጭር ልቦለድ ስብስቦቹ ላይ ‘ይሁዳ’ የሚል ታሪክ አስፍሯል። ልብ ወለዱ የሚያጠነጥነው በተደረገበት መድኃኒት ምክንያት ራሱን የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሆነ ስላመነ ገጸ ባህርይ ነው። ደብተራው ገጸ-ባህርይ አብዝቶ ያስበው፣ ይሰብከው፣ ያስተምረው የነበረውን ሰው ሆነ። ወይም የሆነ መሰለው፡፡ እሱን መሆኑን አመነ። ጌታዬን ሸጥኩ እያለ ተጸጸተ፣… አብረውት ያሉ ተንኮል አሳቢ ሰዎች 30 ብሩን ይመልሱለታል። እናቱን ይቅርታ ይጠይቃል፣ ወዳጆቹን ምህረት ይለምናል።….
የደራሲ እንዳለ ይሁዳ በመጽሐፍ የምናውቀውን ይሁዳ እውነተኛ ታሪክ ሳይተው ወደ አሁን ዘመን አመጣው። በሌላ ሰው ገላ ውስጥ ጨመረው። በይሁዳ በኩል ያለን አመክንዮ በፈጠረው ታሪክ ውስጥ ጨምሮ አቀረበልን። ከጥቁር ሰማይ ስር በሚሰኘው መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ታሪክ ሌሎችም ሸጋ አጭር ልብ ወለዶች ይዟል።
ኧርነስት ረኔ ጽፎት ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም የተረጎሙት ‘የኢየሱስ ሕይወት’ የተሰኘ መጽሐፍ በምድር የኖረውን ኢየሱስ ከታሪክ አንጻር ተመልክቷል። ከመተርጎሙ በፊት በርካታ ውዝግቦችን በእናት ቋንቋው ቢያስተናግድም የአማርኛው ትርጉም ብዙም ተጽእኖ ያሳደረ አልነበረም፡፡ ካህሊል ጅብራን የጻፈው ልብ ወለድም ይሁዳን ከእናቱ ወገን የተመለከተ ነው። የኢየሱስ እናትም የይሁዳ እናትም በእናትነት እኩል ናቸው ሲል እኩይን ከሰናይ አፋጦ የሞገተ ተወዳጅ ሥራው ነው፡፡ የይሁዳ እናት ፍረጂኝ ትላታለች፡፡ የኢየሱስም የይሁዳም እናቶች በእናትነት ለልጆቻቸው እኩል ናቸውና አንባቢን ክፉኛ የመንፈስ ሙግት ውስጥ ያስገባል፡፡
ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ፡ ደግሞ እንደ ጴጥሮስ ይላል። ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ የተባለውን ጴጥሮስን አንስቷል፡፡ ከክህደቱ በኋላ በአፍላው ተጸጽቶ ወደ ቀድሞ እምነቱ የተመለሰውን ጴጥሮስን ባህርይ ከዳችኝ ላላት ሴት ይሰጣል፡፡ እንደቀደሙት ሁሉ ምስለ ኢየሱስ ልንለው የምንችል የአገጣጠም ስልት ነው። ክህደቷን ከኢየሱስ መከዳት ጋር ያስተካክለዋል። የጴጥሮስን ባህርይ ያላብሳታል።
ካንተሌላ ፍጹም ብለሽኝ
እወድሃለሁ ብለሽ ዋሸሽኝ
ሌሊቱ ገና ሳይነጋ
ዓየሁሽ ከሌላ ሰውጋ
አዘነብሽ በቃ ስሜቴ
ስትከጂኝ ሦስቴ
ገጣሚ አበባው መላኩ ‘ከራዲዮን’ በተሰኘ የግጥም ስብስቡ ላይ ያካተተታት አጭር ግጥም ካነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ትዛመዳለች፡፡
አንቺን ነበረ
አበስኩ ገበርኩ ብያለሁ
በጾም ጡትሽን አይቻለሁ
በማማት ስወድቅ ስነሳ
ባንቺ ባየሁት አበሳ
ልቤ ተሰብሮ ካልቀረ
መስቀልስ አንቺን ነበረ
***
በቀራኒዮ ላይ ታየ
በጎሎጎታ ላይ ታየ
የዓለም መድኃኒት የጌታ ትንሳኤ
ብሎ የሚጀምረው የታደሰ ዓለሙ (ነፍስ ይማር) ዘፈን ታሪኩን እና ባህላዊ ክዋኔዎችን አጣምሮ ይተርካል። ከፆሙ ጀምሮ እስከ ሆሳእና፣ ቀራኒዮን፣ ጎሎጎታን፣ የይሁዳን አሳልፎ መስጠት፣ ጸሎተ ሃሙስን፣ 13ቱን ሕማማተ መስቀል፣… ሙሉ ሀይማኖታዊ ታሪኩን ሀይማኖታዊ መልእክትን በሚያስተላልፍ መንገድ ይተርከዋል። ጥቂቶች መዝሙር መሆን ይገባው የነበረ ሃሳብ ከዘፈን ጋር ቀላቅሏል የሚል ሃሳብ ሰንዝረውበታል፡፡ እንደዚሕ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ግን ባህላዊ ክዋኔዎች ከሀይማኖት ሕግጋት ጋር ተዋሕደው ለዘመናት በኖሩበት እንደ ኢትዮጵያ ላለ አኗኗር ተወቃሽ ተግባር አልፈጸመም፡፡ ይልቁንም ሐይማኖታዊ አመጣጡን እና ባህላዊ አከባበሩን በአንድነት አስደመጠን እንጂ…
ለስለስ ባለ ዜማ፣ ባልደመቀ ስልተ-ምት ሲተርክልን የቆየው ዘፈን መካከል ላይ ደመቅ ወዳለ አስጨፋሪ ስልተ ምት ይገባል። የኢየሱስን ህማም፣ ስቃይ፣ መከራ፣ ሞት ተርኮ ሲያበቃ፤ ሰቆቃውን አካፍሎን ሲያበቃ ትንሳኤውን ያበስራል፡፡ የመሲሁን ሞትን ድል የማድረግ ብስራት በውብ ድምጹ ከነገረን በላይ ወደ ፈንጠዝያ ይገባል። ይህም ልከኛ ቅንብር ዘዬ ነው። የግጥሙን እና የዜማውን መንፈስ የማይረብሽ ነው፡፡
ሚሻ ሚሾ ብሎ የሚጀምረው ሁለተኛው የዘፈኑ የዜማ ክፍል ዓለማዊውን ክብረ በዓል ያወሳል። አቶ ስንታየሁ ዓለማየሁ የተባሉ ጸሐፊ ድምጻዊ ታደሰ ዓለሙን የተመለከተ ጽሑፋቸው ሚሻ ሚሾ በተለይ በአገው አካባቢ ያለ፣ በወንዶችም በሴቶችም የሚዘወተር ትውፊታዊ ጨዋታ ነው ሲሉ አስፍረዋል፡፡
የጌታዬ ሰቀላ
ተሸልሟል ባለላ
የመቤቴ አዳራሺ
ተሸልሟል በሻሺ
በዚህኛው ክፍል ባህላዊውን የክብረ በዓል ጎን ሊያሳየን ይጥራል፡፡ የትንሳኤ በዓል ሲከበር ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ብቻ የሚገኙትን የመብል ዓይነቶች አካቷል። ጉልባን የትንሳኤ በዓል ላይ ብቻ የሚገኝ ነውና ‘ከጉልባኑ ይዝገኑ’ ሲል ከጠላው እና ዳቦው ውጪ ያለውን የበዓል አድማቂ ይጠቅሰዋል። ረጅም ጾምን አልፎ የሚገኝ በዓል ነውና ‘ትንሽ ቅቤ፤ ለመገቤ’ አለበት።
እማ ከድፎው
ቢሰጡኝ ቆርሰው
እማ ከጉልባኑ
ይዝገኑ ይዝገኑ
እማ ከዱቄቱ
ትንሽ በወጪቱ…
ማጣፈጫ
መሰልቀጫ
ትንሽ ቅቤ
ለወገቤ
ከጠቀስናቸው የኪነ-ጥበብ ዘውጎች በተጨማሪ በስነ-ስእልም በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ የመጨረሻውን እራት እና ስነ-ስቅለቱን የተመለከቱት ስዕሎች በበርካታ ሰዓሊያን ተስለዋል፡፡ እንደየ እምነታቸው እና የአሳሳል ዘይቤ ፍልስፍናቸው የሚለያዩ ስዕሎችን ለታዳሚው አበርክተዋል፡፡ በዓለም ዙሪያ በብዛት የታወቀው የዳቬንቺ የግድግዳ ላይ ስእል የሆነው የመጨረሻው እራት ነው፡፡ በገዛ ደሟ የሳለችውን ሰዓሊ ደስታ ሃጎስን፣ ገብረክርስቶስ ደስታን ደግሞ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳለ በሰሏቸው ስእሎች እናነሳቸዋለን፡፡ ደምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የገብረክርስቶስ ደስታን ስእል ተመልክቶ “ክርስቶስ ወ ገብረክርስቶስ” የሚል ግጥም ጽፏል።
ዕዩት ይሄን ጠቢብ ሸራው እስኪደማ በቀይ እየወጋ በደም እየሳለው
እንጨት አመሳቅሎ ዳግም ክርስቶስን ጨርቁ ላይ ሰቀለው
ቀራኒዮ ሆነ የወጠረው ሸራ
ጎሎጎታ ሆነ የወጠረው ሸራ
አሁን እስኪመስል ስቃዩ እያስፈራ