ካሌብ መብራቱ ልዩ ድምፁን እና ምርጥ ስራውን በአለምአቀፍ ደረጃ ለመቀጠል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ፕላትፎርም ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር ተፈራረመ።
የልጅነት ሕይወት
አርቲስት ካሌብ መብራቱ( cali cassa) በደሴ፣ ወሎ በ23/12/1996 ዓ.ም ተወለደ። ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ የኢንጂነሪንግ ቢ.ኤስ.ሲ ዲግሪውን ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ አገኘ። ካሊ ካሳ በባሪቶን አና ባስ መካከል ያለ የድምጽ መጠን ያለው ራፐር እና ሙዚቀኛ ሲሆን በዋናኛነት እንደ ጃዝ ራፕ፣ ኦልተርኔቲቭ ሂፕ–ሆፕ፣ ፖፕ ራፕ፣ አርኤንቢ እና ሞምባህቶን በመሳሰሉ ትውፊቶች ላይ እየሰራ ይገኛል።
ከ4ኛ ክፍል ጀምሮ ሁሌም ወደ ሂፕ ሆፕ ሙዚቃ የሚያደላው ካሊ ከታላቅ ወንድሙ ከዲጄ ሳም ጋር በመሆን ለሙዚቃ እውነተኛ ፍቅር አዳበረ። ከዚያም ሙዚቃ በመፍጠር፣ ግጥሞችን አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ እና ላለፉት አሥር ዓመታት በዚህ ሙያ ውስጥ ምን ያህል ጥሩ ውጤት ማግኘት እንደሚችል ለማወቅ በመሞከር ከሙዚቃ ጋር ያለውን ቁርኝት አጠናከረ።
የሙዚቃ ህይወት
ሙዚቀኞች ህዝብ ፊት የማያቀርቧቸው ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳሉ ሁሉ ለካሊ የሙዚቃ ህይወቱ ውስጥ አስቸጋሪ ከሆኑበት ነገሮች ውስጥ ቡድን ማዋቀር፣ መድልዎ፣ ተነሳሸነትን ጠብቆ ማቆየት፣ የአእምሮ ጤና፣ የገንዘብ ፕሮጀክቶች፣ ተሰጦውን ማሳያ መድረኮች ማጣት ፣ የሕትመት መዘግየት እና ፕሮጀክቶችን ማስተዋወቅ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ነበሩ።
“if the shoe fits, wear it and if it looks good, make sure to put it on every day but make sure not to stink it” ካሊ ይህን አባባል በመጠቀም የህይወቱን እያንዳንዱን ደቂቃ ለሙዚቃ መስጠት ችሏል።
ቀደም ሲል በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ሙዚቃን የወደደበት ዋና ምክንያት፣ የማርሻል ብሩስ፣ ሙሉቀን መለስ እና ባህሩ ቃኜ የተለዩ ሙዚቃዎች፣ የካንዬ ዌስት ፈጠራዎች፣ የማሪቱ ለገስ ግሩም ድምፅ፣ የላዎልፍ የዜማ ንድፍ፣ ክቡር ገብረክርስቶስ ደስታ ግጥም እና የህይወት ተሞክሮዎቹ እንደሆኑ ተናግሮ ነበር።
የካሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጥታ ትርኢት ያቀረበው ከ 7 አመት በፊት በ EHHC ራፕ ወድደር ዝግጅት ላይ ሲሆን የመጀመሪያ ክፍያውም 750 ብር ነበር ።
የግል ሕይወት
ካሊ በትርፍ ጊዘውን ግጥም በመፃፍ፣ ተፈጥሮን በማድነቅ፣ ማሰላሰል፣ ሜታፊዚክስ እና ቢብሊዮፊሊስትን በማንበብ እንዲሁም ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ላይ ከአረጋዊያን ጋር ረዥም ውይይት በማድረግ ማሳለፍ ያስደስተዋል። ብዙ ጊዜውን የሚያጠፋው የእጅ ጥበብን በመሥራትና በመሳል ሲሆን ትልቁን የሙዚቃ ትምህርቱን ያገኘበት ጊዜ ለስራው ፈር ቀዳጅ ከሆኑ ሰዎች ኣንዱ ከሆነው ሁናንተ ሙሉ ጋር እየሰራ በነበረበት ጊዜ ነው ።
በአድማጮቹ ላይ እውነተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር በማሰብ የሚሰራባቸውን የሙዚቃ ቋንቋዎች በትክክል ለመረዳት ጊዜ ወስዶ ይሰራል። ስለዚህ ሙዚቃው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅና የሚያነቃቃ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን የያዘ በመሆኑ በህዝቡ ልብ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል። ወደ ክለቦች ከመሄድ ይልቅ በጫካ ውስጥ ብቻውን በባዶ እግሩ መራመድ እንደሚወድ የሚናገረው ካሊ ከውሻ እና ድመቶች ይልቅ ጦጣ እና ድብ እንደ የቤት እንስሳ እንደሚመርጥም ተናግሯል።
ካሊ ወደፊት ከታላላቅ አርቲስቶች ጋር በመተባበር በመላው ዓለም ራሱን የሚወክል ቤተሰብ እና ደጋፊ እንዲኖረው እንዲሁም በሙያው የተለያዩ ሽልማቶችን ማግኘት፣ እና የተሟላ የዲስኮግራፊ መብት ያለው ራሱን የቻለ ሠዓሊ መሆን ይፈልጋል።
ከሰዋሰው ጋር
በአሁኑ ወቅት ከሰዋሰው መልቲመዲያ ጋር በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ሊለቀቅ የታሰበ አልበሙ ላይ እየሰራ ሲሆን ብሩህ እና ፍሬያማ ጉዞ ከሰዋሰው ጋር እንደሚኖረው በማሰብ ስምምነቱን ኣንደፍጸመ ተናግሯል።