የአስቴር አወቀ “ሶባ” አልበም የመውጫ ቀን ለ9 ቀናት ተራዘመ

ቀን / Date : ጥር 9/2015 ዓ.ም.

ለ ሚዲያ ተቋማት

ከ1970ዎቹ ጀምሮ የሙዚቃ ንግሥትነቷን አስጠብቃ የቆየችው አስቴር፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ የራሳቸውን ጉልህ አሻራ ካሳረፉ ድምጻዊያን መካከል ትመደባለች። በየዘመናቱ በነበሩት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማለትም፡- በሸክላ፣ በካሴት እና በሲዲ ስራዎቿን ለአድናቂዎቿ ስታደርስ ቆያታለች። በብዙዎች ዘንድም “የሶል ንግሥት” የሚል የፍቅር ስያሜ አግኝታለች።

“ሶባ” የተሰኘው አልበሟም ዘመን በወለደው የቴክኖሎጂ ውጤት በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል በጥምቀት ዋዜማ እንደሚለቀቅ በሰፊው ተነግሯል። ይሁን እንጂ ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚወጣ ፕሮግራም የተያዘለት “ሶባ” አልበም የመውጫ ጊዜው ተራዝሟል።

በከፍተኛ ጥራት የተዘጋጀው “ሶባ” የሙዚቃ አልበም መውጫ ቀን የተራዘመው ከአልበሙ ጋር በጋራ እንዲለቀቅ የታሰበው የሙዚቃ ቪድዮ ዝግጅቱ ባለመጠናቀቁ ነው። በአስቴር “ሶባ” አልበም ከተካተቱት 10 ስራዎች መካከል አንዱ በምስል እየተቀናበረ በመሆኑ እና የቪድዮው ዝግጅት ከታሰበበት ጊዜ በላይ በመውሰዱ የአልበሙ የመውጫ ቀን እንዲራዘም አስገድዷል።

seawsew artist aster aweke soba album

ብዙዎች የሚጓጉለት፣ በከፍተኛ ጥራት የተዘጋጀው የአስቴር አወቀ “ሶባ” አልበም የመውጫ ቀን የፊታችን አርብ ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ሆኗል። አልበሙ ቀድሞ በወጣለት መርሃግብር ለአድማጭ እንዳይደርስ ያስገደደው የሙዚቃ ቪድዮ ባይጠናቀቅ እንኳን የጥር አስራ ዘጠኙ ፕሮግራም የማይታጠፍ እንደሆነ ሰዋሰው ሊያሳውቅ ይወዳል። ለተፈጠረው መዘግየት ሰዋሰው መተግበሪያ አስቴር አወቀን እና አድናቂዎቿን እንዲሁም አጠቃላይ የሙዚቃ ወዳጆችን ይቅርታ ይጠይቃል። ሰዋሰው የአስቴር አወቀን “ሶባ” አልበም ለአድማጭ ሲያደርስ ለኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪው አዲስ ምዕራፍ እንደሚያበስር በዚህ አጋጣሚ ያሳውቃል።

ሰዋሰው መልቲ ሚድያ

ጥር 9 ቀን 2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ

ለበለጠ መረጃ  በስ.ቁ 0911 56 36 67 / 0913 99 73 05 ይደውሉ

Sewasew Multimedia Logo
Igniting Creativity

Sewasew is a global Ethiopian music streaming platform which is aimed to bring fans closer to artists through unique experiences and the highest sound quality

Contact Us

Download APP